ታላቁና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።
የሰማይ ከዋክብትና ሰራዊታቸው፣ ብርሃን አይሰጡም፤ ፀሓይ ገና ከመውጣቷ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።
የተማረከ ሁሉ ይወጋል፤ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።
እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ጨካኝ ነው፤ ምድርን ባድማ ሊያደርጋት፣ በውስጧም ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፣ ከመዓትና ከብርቱ ቍጣ ጋራ ይመጣል።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣ በሽማግሌዎቹም ፊት በክብሩ ይነግሣል፤ ጨረቃ ትሸማቀቃለች፤ ፀሓይም ታፍራለች።
እግዚአብሔር የበቀል ቀን፣ ስለ ጽዮንም የሚሟገትበት ዓመት አለውና።
ምድርን ተመለከትሁ፤ እነሆ ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች፤ ሰማያትንም አየሁ፣ ብርሃናቸው ጠፍቷል።
በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በቅዱሱ ተራራዬም የማስጠንቀቂያውን ድምፅ አሰሙ። በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤ እርሱም በደጅ ነው።
ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፤ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች።
ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ፣ ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ ተሰብስቧል፤ ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ፣ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና።
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን፣ ፀሓይ በቀትር እንድትጠልቅ አደርጋለሁ፤ ምድርንም ደማቅ ብርሃን ሳለ በቀን አጨልማታለሁ።
“እነሆ፤ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ።
“ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናጋሉ።’
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።
“በዚያ ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤
“በፀሓይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክት ይሆናል፤ ከባሕሩና ከሞገድ ድምፅ የተነሣ፣ በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ይጨነቃሉ፤ ይታወካሉም።
በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣ አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ ይሆናል።
የጌታን ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’
ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ።
ምክንያቱም እንደ ሌባ እንዲሁ የጌታ ቀን በሌሊት እንደሚመጣ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።
የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል።
በዚያው ቃል ደግሞ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል።
አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሓይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሓይም ሰዎችን በእሳት እንድታቃጥል ኀይል ተሰጣት።
ስድስተኛውን ማኅተም ሲፈታ ተመለከትሁ፤ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሓይም እንደ ማቅ ጠቈረች፤ ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች።