ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው።
አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና።
እርሱ የግብጽ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብጽን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል።
በድርጊታችሁና በብልጽግናችሁ ስለምትታመኑ፣ እናንተም ትማረካላችሁ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋራ፣ በምርኮ ይወሰዳል።
አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብጽም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋራ ከመዋጋት ይቈጠባል።
የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል።
እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቍረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።