ዳዊት ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ ንጉሡም ቤቱን እንዲጠብቁ ትቷቸው የሄደውን ዐሥሩን ቁባቶቹን ወሰደ፤ በአንድ ቤትም ውስጥ እንዲጠበቁ አደረገ። ቀለብ ሰጣቸው፤ ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ አልገባም ነበር፤ እነርሱም እስከ ሞቱበት ጊዜ ድረስ መበለት ሆነው፣ ለብቻቸው ተገልለው ተቀመጡ።
በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው።
ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋራ ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ።
ስለዚህ የእስራኤል ሰው ሁሉ ዳዊትን ከድቶ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተለ። የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንሥቶ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ከንጉሣቸው ሳይለዩ ዐብረውት ሄዱ።