ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።
እግዚአብሔርም ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።
ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የእግዚአብሔርም መላእክት ተገናኙት፤
ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ፣ “ይህ የእግዚአብሔር ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦታ ስም መሃናይም አለው።
ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤
እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ።
የእልፍኝህን አግዳሚ በውሆች ላይ አኖርህ፤ ደመናትን ሠረገላህ አደረግህ፤ በነፋስ ክንፍ ትሄዳለህ።
መላእክትህን መንፈስ፣ አገልጋዮችህንም የእሳት ነበልባል ታደርጋለህ።
ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት።
ተራሮች ኢየሩሳሌምን እንደ ከበቧት፣ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው።
እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም።
የእግዚአብሔር ሠረገላዎች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ ሺሕ ጊዜም ሺሕ ናቸው፤ ጌታ ከሲና ወደ መቅደሱ ገባ።
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤
ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ።
የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ።
ራእዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርሁ፤ ከእኔ ጋራ የነበሩት ሰዎች አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ፍርሀት ስለ ወደቀባቸው ሸሽተው ተደበቁ።
በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጧል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም ቀይ፣ ቡናማና ነጭ ፈረሶች ነበሩ።
በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ።
ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድድልኝ ይመስልሃል?
አንተም ዐይናቸውን ትከፍታለህ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ።’
እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?
ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም።
የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።
“በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፣ የዳዊትንም መክፈቻ በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም፤ የዘጋውንም ማንም ሊከፍተው አይችልም።