ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ ዐብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጧል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው።
ከዚያም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ፣ በጾምና በጸሎት ላመኑበት ጌታ ዐደራ ሰጧቸው።
በዚህ ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ቤተ ክርስቲያን ጋራ ሆነው ከመካከላቸው አንዳንድ ሰዎችን መርጠው፣ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋራ ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ ከወንድሞችም መካከል ዋነኛ የነበሩትን በርስያን የተባለውን ይሁዳንና ሲላስን መረጡ፤
ስለዚህ ጥቂት ሰዎች መርጠን ከተወዳጆቹ ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋራ ወደ እናንተ ለመላክ ሁላችንም ተስማምተናል፤
ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ።
ወዲያውም በከተማው ሁሉ ሁከት ተነሣ፤ ሕዝቡም አንድ ላይ በማበር የመቄዶንያ ተወላጅ የሆኑትንና ከጳውሎስ ጋራ ይጓዙ የነበሩትን ጓደኞቹን፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ እየሮጡ ገቡ።
ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን።
ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኗል።
አሁንም የጀመራችሁትን ተግባር በዐቅማችሁ መጠን ከፍጻሜ አድርሱት፤ ይህም ለመስጠት የነበራችሁ በጎ ፈቃድ እውን እንዲሆን ነው።
ለመስጠት በጎ ፈቃድ ካለን ስጦታው ተቀባይነት የሚያገኘው ባለን መጠን ስንሰጥ እንጂ፣ በሌለን መጠን ለመስጠት ስንሞክር አይደለም።
በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን።
ምክንያቱም ሌሎችን ለመርዳት ያላችሁን በጎ ፈቃድ ዐውቃለሁ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እናንተ በአካይያ የምትኖሩ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንደ ሆናችሁ ለመቄዶንያ ሰዎች አፌን ሞልቼ ተናግሬአለሁ፤ ቅን ፍላጎታችሁም ብዙዎችን ለበጎ ሥራ አነሣሥቷል።
ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤