መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።
ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”
ወደ ላይ ነጥቀህ በነፋስ ፊት አበረርኸኝ፤ በዐውሎ ነፋስም ወዲያ ወዲህ ወዘወዝኸኝ።
ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፣ መሠረታቸው ከዐፈር የሆነ፣ ከብልም ይልቅ በቀላሉ የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?
ወደ አንተ በተጣራሁ ቀን፣ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ በዚህም፣ አምላክ ከጐኔ መቆሙን ዐውቃለሁ።
ቤቴ እንደ እረኛ ድንኳን ተነቀለ፤ ከእኔም ተወሰደ፤ ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤ ከመጠቅለያ ቈርጦኛል፤ ከጧት እስከ ማታ ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።
“ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።”
“ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤
እኛ የእግዚአብሔር የሆንን ዐብሮ ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።
ነገር ግን ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።
በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም።
በርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤
መከራን የምቀበለውም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም ያመንሁትን እርሱን ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም ዐደራ እስከዚያች ቀን ድረስ መጠበቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ።
ምክንያቱም መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።
ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ፣ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ።
ክርስቶስ የእውነተኛዪቱ ድንኳን ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደ ተሠራችው መቅደስ አልገባም፤ ነገር ግን አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት ወደ እርሷ፣ ወደ ሰማይ ገባ።
እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን።
እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤
ወንድሞቻችንን ስለምንወድድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል።
እኛ ከእውነቱ መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፤
ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለን፤ እርሱን እንደምንመስልም እናውቃለን።