እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤ በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።
ሐሰተኛ ትንቢት ስለሚነግሯችሁ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሙ፤
“አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤
አንዳንድ ሰዎችም ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው፣ “በሙሴ ሥርዐት መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም” በማለት ወንድሞችን ማስተማር ጀመሩ።
አንዳንድ ሰዎች ያለ እኛ ፈቃድ ከእኛ ዘንድ ወጥተው በንግግራቸው ልባችሁን እንዳወኩና እንዳናወጧችሁ ሰምተናል።
ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ።
እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ሆድ ነው። በለሰለሰ አንደበታቸውና በሽንገላ የዋሆችን ያታልላሉ።
እንግዲህ የርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
እኛ እኮ ትርፍ ለማግኘት ብለን የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ሰዎች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት እንናገራለን።
ነገር ግን ስውርና አሳፋሪ ነገሮችን ትተናል፤ በማታለል አንመላለስም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሐሰት ጋራ አንቀላቅልም፤ ይልቁንም እውነትን በግልጽ እየተናገርን በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን።
እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።
ይህ ጕዳይ የተነሣው አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ነጻነት ሊሰልሉና ባሪያዎች ሊያደርጉን ወደ እኛ ሾልከው በመግባታቸው ነው።
እነዚያ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሊወስዷችሁ ይተጋሉ፤ ለበጎ ግን አይደለም፤ የሚፈልጉት እናንተን ከእኛ ነጥለው የራሳቸው ሊያደርጓችሁ ነው።
ውጫዊ በሆነ ነገር ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ትገረዙ ዘንድ ሊያስገድዷችሁ ይጥራሉ፤ ይህንም የሚያደርጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ነው።
ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም።
ምክንያቱም ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደ ነገርኋችሁ፣ አሁንም እንደ ገና፣ ያውም በእንባ እነግራችኋለሁ፤ ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ።
ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ።
ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ።
በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ወግና በዚህ ዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።
ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደ ሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።
ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።
ከረዥም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኩሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።
ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከርሱም ጋራ በፊቱ ምልክቶችን ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ። በእነዚህ ምልክቶች የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አሳተ። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ተጣሉ።
ሥራህን፣ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ። ክፉዎችንም ችላ ብለህ እንዳላለፍሃቸው፣ ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትንም መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ።
ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ነቢይ ነኝ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለሃታል፤ እርሷ ባሮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በትምህርቷ ታስታቸዋለች።
መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን እያሉ ስምህን የሚያጠፉትን ዐውቃለሁ፤ እነርሱ ግን የሰይጣን ማኅበር ናቸው።