እንዲህ የሚሉ ሰዎች በሩቅ ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን ሁሉ በቅርብ ሆነን በተግባራችን የምንገልጸውም እንደዚያው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።
አንዳንዶች፣ “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይላሉ።
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ሰዎች ጋራ ራሳችንን ልንመድብ ወይም ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመዝኑና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋራ ሲያነጻጽሩ አስተዋዮች አይደሉም።
ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባትም በመካከላችሁ ጥል፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ አድመኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜት፣ እብሪትና ሁከት ይኖራል ብዬ እሠጋለሁ።
ከእናንተ ርቄ ሳለሁ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ሥልጣኔን በኀይል እንዳልጠቀም ነው፤ ጌታም ይህን ሥልጣን የሰጠኝ እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም።