ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ አንሥቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ ስለማያውቅ፣ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ።
ንጉሥ ሕዝቅያስና ሹማምቱ፣ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። እነርሱም ውዳሴውን በደስታ ዘመሩ፤ ራሳቸውንም አጐንብሰው ሰገዱ።
ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ እግዚአብሔርም ሰማቸው፤ ጸሎታቸውም ወደ ሰማይ ወደ ቅዱሱ ማደሪያው ደረሰ።
ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋራ እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም።
ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር።