አምላካችን ሆይ፤ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳድደህ ያስወጣህና ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘላለም የሰጠሃቸው አንተ አይደለህምን?
እግዚአብሔርም ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ።
ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ።
በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋራ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ እሆናለሁ።
በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ደካሞችን ከኀይለኞች የሚታደግ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።”
እነርሱም ተቀመጡባት፤ ለስምህ መቅደስ ሠሩባት፤ እንዲህም አሉ፤
ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርጌሳውያንን ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ።
ሕዝቦችን በእጅህ አሳድደህ አወጣሃቸው፤ አባቶቻችንን ግን ተከልሃቸው፤ ሕዝቦችን አደቀቅህ፤ አባቶቻችንን ግን ነጻ አወጣሃቸው።
ምድሪቱን የወረሱት በሰይፋቸው አልነበረም፤ ድልንም የተጐናጸፉት በክንዳቸው አይደለም፤ አንተ ወድደሃቸዋልና ቀኝ እጅህ፣ ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አደረገ።
ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባርረህ እርሷን ተከልሃት።
“ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
መልአክን በፊትህ በመላክ፣ ከነዓናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያዊያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ።
የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብጻውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ።
“አንተ ግን፣ ባሪያዬ እስራኤል፣ የመረጥሁህ ያዕቆብ፣ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፤
ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው።
ከእንግዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚሠራውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጽሁላችሁ ወዳጆች ብያችኋለሁ።
ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ከፊትህ በማስወጣት ወደ ምድራቸው አስገብቶህ ለአንተ ርስት አድርጎ ለመስጠት ነው።
“አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ።
“ጽና፤ ለቀደሙት አባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር እንዲወርሱ፣ ይህን ሕዝብ የምትመራው አንተ ነህና በርታ።
“እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቷቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።
ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’
እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይሥሐቅንም ሰጠሁት።