እርሱም አሳን ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አሳ፣ እናንተም ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፤ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋራ ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋራ ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን፣ ይተዋችኋል።
ሃዳድ ካስከተለበት ችግር ሌላ ሬዞን በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ሌላው የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ ሬዞን ሶርያን ገዛ፤ እስራኤልንም ይጠላ ነበር።
ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ።
የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ።
“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
በየከተሞቹም ሁሉ ጋሻና ጦር አከማችቶ ይበልጥ አጠናከራቸው። በዚህ ዐይነት ይሁዳንና ብንያምን የራሱ አደረገ።
ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ ይሁዳ መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።
እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ መሪያችንም እርሱ ነው። መለከት የያዙ ካህናቱም የጦርነቱን ድምፅ በእናንተ ላይ ያሰማሉ። እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ አይቀናችሁምና፣ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋራ አትዋጉ።”
አብያ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ፣ እንዲህ አለ፤ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ስሙኝ!
በፍጹም ልባቸው ስለ ማሉም የይሁዳ ሕዝብ በመሐላው ደስ ተሠኙ። እግዚአብሔርን ከልብ ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጣቸው።
በመከራቸው ጊዜ ግን፣ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው።
እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡ።
ይህን ጦርነት የምትዋጉት እናንተ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁንም ማዳን እዩ። አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገውኑ ውጡና ግጠሟቸው፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋራ ይሆናል።’ ”
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።
የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቷችኋል’ ” አላቸው።
እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።
ከእነርሱ ጋራ ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋራ ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።
ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት።
በተጨነቀም ጊዜ የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።
በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ፣ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ።
“መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቍጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።
እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።
የሚያስተውል፣ እግዚአብሔርን የሚፈልግ እንዳለ ለማየት፣ እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ሰው ልጆች ተመለከተ።
በጨለማ ምድር፣ በምስጢር አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብም ዘር፣ ‘በከንቱ ፈልጉኝ’ አላልሁም። እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ፤ ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለሁ።
“እናንተ ጽድቅን የምትከታተሉ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉ ስሙኝ፤ ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣ ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጕድጓድ ተመልከቱ።
ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ! የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን?
በመንገድ የሚመራሽን፣ እግዚአብሔር አምላክሽን በመተውሽ፣ ይህን በራስሽ ላይ አላመጣሽምን?
በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፣ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ ከዚያ በኋላ እንደ ተናገራችሁት፣ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሆናል።
ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ስላይደለ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ፤
አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በዚያ ያጋጥሟችኋልና። እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁትና እርሱም ከእናንተ ጋራ ስለማይሆን በሰይፍ ትወድቃላችሁ።”
ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”
ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና።
በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን ከእኛ ጋራ ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ።
ነገር ግን እዚያም ሆናችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ብትፈልጉት ታገኙታላችሁ።
ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በርሱ ደስ አትሰኝም።”
የሚናገረውን እርሱን እንቢ እንዳትሉት ተጠንቀቁ። እነዚያ ከምድር ሆኖ ሲያስጠነቅቃቸው የነበረውን እንቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፣ እኛ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ከርሱ ብንርቅ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?
ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።
የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም፣ የሮቤልን የጋድንና የምናሴን ወገኖች “በዚህ ነገር እግዚአብሔርን አልበደላችሁምና፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ መሆኑን ዛሬ ዐውቀናል፤ እነሆ እስራኤላውያንን ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል” አላቸው።
እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።”
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል የሚነሣም በሁለተኛው ሞት ከቶ አይጐዳም።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ ደግሞም ከሚቀበለው ሰው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይ እሰጠዋለሁ።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን፣ ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል ለሚነሣ በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ አደርገዋለሁ።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”
እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤
ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ “የሴኬም ገዦች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ።
እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዞቹ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።
እግዚአብሔርን የማትታዘዙና በትእዛዞቹም ላይ የምታምፁ ከሆነ ግን፣ እጁ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ነበረች ሁሉ በእናንተም ላይ ትሆናለች።