ያ ሰው በትዕቢት ተወጥሯል፤ አንዳችም አያስተውልም። ስለ ቃላት ለመከራከርና ለመጣላት ክፉ ጕጕት አለው፤ እነዚህም ቅናትን፣ ጥልን፣ ስድብን፣ መጥፎ ጥርጣሬን ያስከትላሉ፤
ምንም ሳይኖረው ባለጠጋ መስሎ የሚታይ ሰው አለ፤ ሌላው ድኻ መስሎ ይታያል፤ ግን ብዙ ሀብት አለው።
የማይለግሰውን ስጦታ እቸራለሁ ብሎ ጕራ የሚነዛ ሰው፣ ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው።
ራሱን እንደ ጠቢብ የሚቈጥረውን ሰው አይተሃልን? ከርሱ ይልቅ ለሞኝ ተስፋ አለው።
ጾማችሁ በጥልና በክርክር፣ በግፍ ጡጫና በመደባደብ ይፈጸማል፤ ከእንግዲህ ዛሬ እንደምትጾሙት ጾማችሁ፣ ድምፃችሁ ወደ ላይ እንደሚሰማ ተስፋ አታድርጉ።
ይህም ጳውሎስንና በርናባስን ከእነርሱ ጋራ ወደ ከረረ ጠብና ክርክር ውስጥ ከተታቸው። ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ ከሌሎች አንዳንድ ምእመናን ጋራ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ስለዚሁ ጕዳይ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን እንዲጠይቁ ተወሰነ።
ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ በመሆኑ፣ እናንተው ጨርሱት፤ እኔ በእንዲህ ዐይነት ነገር ፈራጅ ለመሆን አልሻም።”
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር።
እርስ በርሳችሁ በአንድ ሐሳብ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋራ ዐብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ።
በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን።
በእምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው፣ አከራካሪ በሆኑ ጕዳዮች ላይ በአቋሙ ሳትፈርዱበት ተቀበሉት።
ነገር ግን በራስ ወዳዶች፣ እውነትን ትተው ክፋትን በሚከተሉ ፍርድና ቍጣ ይደርስባቸዋል።
እንግዲህ ማንም በዚህ ጕዳይ ላይ መከራከር ቢፈልግ፣ እኛም ሆንን የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።
ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ።
ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ራሱን እንደ ሞኝ ይቍጠር።
አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ። ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን?
ማንም ተነሥቶ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ቢበዘብዛችሁ፣ ለጥቅሙ ሲል ቢጠጋችሁ፣ ቢንቀባረርባችሁ ወይም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ።
ነገር ግን እርስ በርሳችሁ የምትነካከሱና የምትበላሉ ከሆነ፣ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
እርስ በርሳችን እየተጐነታተልንና እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ።
አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ትልቅ የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላል።
አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ።
ማንኛውንም ነገር ሳታጕረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤
ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።
ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤
እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል።
ደግሞም ለተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልዶች ታሪክ ራሳቸውን አሳልፈው እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እነዚህ ነገሮች በእምነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሥራ ይልቅ ክርክርን ያነሣሣሉ።
የሕግ መምህራን ለመሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ስለሚናገሩት ወይም አስረግጠው ስለሚሟገቱለት ነገር አያውቁም።
በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ በወደቀበት ፍርድ እንዳይወድቅ አዲስ ክርስቲያን አይሁን።
ስለ እነዚህ ነገሮች ማሳሰብህን አትተው፤ በቃላት እንዳይነታረኩ በእግዚአብሔር ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ ጥቅም የሌለው፣ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና።
ከማይረባና ትርጕም የለሽ ከሆነ ክርክር ራቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ጠብን እንደሚያስከትሉ ታውቃለህ።
ከዳተኞች፣ ችኵሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወድዱ ይሆናሉና።
ነገር ግን ከንቱ ከሆነ ክርክርና ከትውልድ ሐረግ ቈጠራ፣ ከጭቅጭቅና ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ፤ ይህ ዋጋ ቢስና ከንቱ ነውና።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህን አስተውሉ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤
እነዚህ ሰዎች ግን ምንም በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ፤ እነርሱም ለመያዝና ለመገደል እንደ ተወለዱ፣ በደመ ነፍስ እንደሚመሩና አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት የሚጠፉ ናቸው።
ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና።
እነዚህ ሰዎች ግን የማያውቁትን ነገር ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት በደመ ነፍስ በሚያውቁት ነገር ይጠፋሉ።
እነዚህ ሰዎች የሚያጕረመርሙና ሌሎችን ሰዎች የሚከስሱ ናቸው፤ ክፉ ምኞቶቻቸውን ይከተላሉ፤ በራሳቸው ይታበያሉ፤ ጥቅም ለማግኘት ሲሉም ሌሎችን ይክባሉ።
‘ሀብታም ነኝ፣ ባለጠጋ ነኝ፣ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም።