ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ምድር አንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀመጠ።
በዚያ ጊዜም ዳዊትና ሰዎቹ ወጥተው ጌሹራውያንን፣ ጌርዛውያንንና አማሌቃውያንን ወረሩ። እነዚህ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ፣ እስከ ሱርና እስከ ግብጽ ባለው ምድር ላይ ይኖሩ ነበር።
የፍልስጥኤም አዛዦችም፣ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን እያደረጉ ነው?” ብለው ጠየቁ። አንኩስም፣ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የነበረው ዳዊት አይደለምን? ከእኔ ጋራ መኖር ከጀመረ እነሆ ዓመት ዐለፈው፤ እኔን ከተጠጋበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም በደል አላገኘሁበትም” አላቸው።