እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
ከስድሳ ሁለቱ ሱባዔ በኋላ መሲሑ ይገደላል፤ ምንም አይቀረውም። የሚመጣው አለቃ ሰዎችም፣ ከተማውንና ቤተ መቅደሱን ይደመስሳሉ። ፍጻሜውም እንደ ጐርፍ ይመጣል፤ ጦርነት እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፤ ጥፋትም ታውጇል።
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ እነሆ፤ ጻድቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣ ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል።
ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣
በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለ ተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት።
ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ።
ስለ ጽድቅ፣ ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤
“እርሱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ቃሉን ከአንደበቱ እንድትሰማ መርጦሃል፤
ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤
በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እርሱ ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ።
በርሱም በኩል አሁን ወደ ቆምንበት ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ተስፋ በማድረግ ሐሤት እናደርጋለን።
ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል።
ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ፤
ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለ ሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋራ እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም።
የተሰቀለው በድካም ቢሆንም፣ በእግዚአብሔር ኀይል ሕያው ሆኖ ይኖራል። እኛም በርሱ ደካሞች ብንሆንም፣ እናንተን ለማገልገል ግን በእግዚአብሔር ኀይል ከርሱ ጋራ ሕያዋን ሆነን እንኖራለን።
እኛ በርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።
እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ፣ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን ሰጠ፤
“በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል።
በርሱና በርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን።
እርሱም ከክፋት ሊቤዠን፣ መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋውን የርሱ የሆነውን ሕዝብም ለራሱ ያነጻ ዘንድ ራሱን ስለ እኛ ሰጥቷል።
በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል።
በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጧል።
ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኗል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።
እናንተን ያልተቃወሙትን ንጹሓን ሰዎች ኰንናችኋል፤ ገድላችኋልም።
በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው።
እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቷል።
ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።
ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃም ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው።