ሰሎሞን፣ “ባለብዙ ምሰሶ አዳራሽ” የተባለ ቤት ሠራ፤ የዚህም ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሠላሳ ክንድ፣ ነበር፤ በስተ ፊት በኩልም ጣራ ያለውና በአዕማድ የተደገፈ መመላለሻ ነበረው።
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ከመመላለሻ በረንዳው ጭምር እንደ ትልቁ አደባባይ አምሮ በተጠረበ ሦስት ረድፍ ድንጋይና ተስተካክሎ በተከረከመ በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ የታጠረ ነበር።
በሮቹ በሙሉ ባለአራት ማእዘን መቃኖች ያሏቸው፣ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ።