በመመላለሻው ምሰሶዎች ዐናት ላይ ያሉት ጕልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው።
የቤተ መቅደሱም፣ ውስጡ በሙሉ በዝግባ የተለበጠ ሲሆን፣ ይህም በእንቡጥ አበቦችና በፈኩ አበቦች ቅርጽ የተጌጠ ነበር፤ በሙሉ ዝግባ እንጂ የሚታይ ድንጋይ አልነበረም።
ደግሞም በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን ጕልላቶች ለማስጌጥ የእያንዳንዱን መረብ ዙሪያ የሚከብቡ ሮማኖች በሁለት ረድፍ ሠራ፤ ለሁለቱም ጕልላቶች ያደረገው ተመሳሳይ ነበር።
በሁለቱም የምሰሶ ጕልላቶችና ከመርበቡ ቀጥሎ ባለው የክብ ቅርጽ ላይ ዙሪያውን በሙሉ ሁለት መቶ ሮማኖች በተርታ ነበሩ።
ዐናቱ ላይ ያሉት ጕልላቶች የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ።