እኛ ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን፣ መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን።
እንዲህም አለው፤ “የእነዚህ መንግሥታት ሥልጣንና ክብር ሁሉ ለእኔ ተሰጥቷል፤ እኔም ለምወድደው ስለምሰጥ፣ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤
ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል።
የዚህ ዓለም ገዥ ስለሚመጣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋራ ብዙ አልናገርም። እርሱም በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፤
ስለ ፍርድም፣ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።
የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም።
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል።
እንግዲህ ትምክሕታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋራ ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደ ኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው።
የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሯል።
መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።
እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ፣ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን ሰጠ፤
በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።
መከራን የምቀበለውም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም ያመንሁትን እርሱን ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም ዐደራ እስከዚያች ቀን ድረስ መጠበቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ።
ቀደም ሲል እኛ ራሳችን ማስተዋል የጐደለን፣ የማንታዘዝ፣ የተታለልን፣ ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ ሆነን የተገዛን ነበርን፤ እየተጣላንና እርስ በርስ እየተጠላላን በክፋትና በምቀኛነት እንኖር ነበር።
አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋራ ወዳጅነት ከእግዚአብሔር ጋራ ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል።
ወንድሞቻችንን ስለምንወድድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል።
ትእዛዞቹንም የሚጠብቁ ሁሉ በርሱ ይኖራሉ፤ እርሱም በእነርሱ ይኖራል። በእኛ መኖሩን በዚህ፣ ይኸውም እርሱ በሰጠን መንፈስ እናውቃለን።
በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሁሉ በልቡ ምስክር አለው፤ ማንም እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።
በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ እናንተ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤
የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን፣ የለመንነውንም ነገር እንደ ተቀበልን እናውቃለን።
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአት እንደማያደርግ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚጠብቀው፣ ክፉውም እንደማይነካው እናውቃለን።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከርሱ ጋራ ተጣሉ።
ሺሑ ዓመት እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።