እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ።
እግዚአብሔርም፣ “የምትወድደውን አንዱን ልጅህን፣ ይሥሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው።
የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤
“አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወድደው ልጁ ነበረ፤ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው።
“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣
ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና።
በርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል።
ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው።
ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”
ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል።
የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋራ ነው፤ ምን ጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እርሱ ላከኝ እንጂ በገዛ ራሴ አልመጣሁም።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው።
ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከርሱ ጋራ እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?
እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ወይስ ደግሞ፣ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።
ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኀጢአታችን ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው።
ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በርሱ ይኖራል።
ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው።
በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ እናንተ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤