ለመሆኑ፣ አንተን ከሌላው እንድትበልጥ ያደረገህ ማን ነው? ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ?
እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።
እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። “ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ። “የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።
“ንጉሥ ሆይ፤ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትንና ታላቅነትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው።
ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ፣ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቍባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ፣ የናስና የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም።
ከባሮቹም መካከል ዐሥሩን ወደ ራሱ ጠርቶ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱበት’ አላቸው።
ከርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤
ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም።
በርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ።
እንደ ተሰጠን ጸጋ የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ለአንዱ የተሰጠው ስጦታ ትንቢት መናገር ከሆነ፣ እንደ እምነቱ መጠን ይናገር።
ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋራ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።
ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው።
መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁምን?
ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ምኞቴ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለው የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው።
በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም።
እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል።