እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውስጣችሁ እንደሚኖር አታውቁምን?
መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ።
እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ ዐብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ።
ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምትታዘዙት ለርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?
ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋራ አንድ እንድንሆን የተጠመቅን ሁላችን፣ ከሞቱ ጋራ አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?
ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል።
እናንተ ግን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ፣ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ናችሁ። ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፣ እርሱ የክርስቶስ አይደለም።
ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ።
እኛ የእግዚአብሔር የሆንን ዐብሮ ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።
መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁምን?
ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋራ የሚተባበር ሰው ከርሷ ጋራ አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን? “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ተብሏልና።
ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤
ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣
በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን?
በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ።
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋራ ምን ስምምነት አለው? እኛ እኮ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ “ከእነርሱ ጋራ እኖራለሁ፤ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”
ይህንም የምጽፍልህ ብዘገይ እንኳ ሰዎች በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንድታውቅ ነው፤ ቤቱም የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው።
የተሰጠህን መልካሙን ዐደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።
ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን።
አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋራ ወዳጅነት ከእግዚአብሔር ጋራ ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል።
እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ።
እግዚአብሔርን ያየ ከቶ ማንም የለም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ ግን እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል።