ከዚህም በቀር ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሣ፣ ለዚህ ለተቀደሰ ቤት ከዚህ በፊት ከሰጠሁት በተጨማሪ፣ ለዚሁ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብር እሰጣለሁ፤
ኢዮአስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሕዝብ ቈጠራ የተገኘውንና በስእለት የገባውን እንዲሁም በራስ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ቤት የተሰጠውን የተቀደሰ ገንዘብ በሙሉ ሰብስቡ።
ንጉሥ ዳዊት ግን ኦርናን “እንዲህ አይደረግም፤ ሙሉውን ዋጋ እኔ እከፍላለሁ፤ የአንተ የሆነውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ አልፈልግም፤ ዋጋ ያልከፈልሁበትንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” ሲል መለሰለት።
እኔም ያለኝን ሀብት ለአምላኬ ቤተ መቅደስ ለወርቁ ሥራ ወርቁን፣ ለብሩ ሥራ ብሩን፣ ለናሱ ሥራ ናሱን፣ ለብረቱ ሥራ ብረቱን፣ ለዕንጨቱ ሥራ ዕንጨቱን እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን መረግድ፣ ኬልቄዶን፣ ልዩ ልዩ ኅብር ያላቸውን የከበሩ ድንጋዮች፣ ማንኛውንም ዐይነት የሚያምር ድንጋይና ዕብነበረድ፣ ይህን ሁሉ በብዛት አዘጋጅቻለሁ።
ይህም ሦስት ሺሕ መክሊት የኦፊር ወርቅና ሰባት ሺሕ መክሊት ንጹሕ ብር ለቤተ መቅደሱ የግድግዳ ግንብ ማስጌጫ
እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣ የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማደሪያህ ምንኛ የተወደደ ነው!
በሌላ ስፍራ ሺሕ ቀን ከመኖር፣ በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል፤ በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፣ በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ።
“ስጦታ እንዲያመጡልኝ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። ይሰጥ ዘንድ ልቡ ካነሣሣው ከእያንዳንዱ ሰው ስጦታን ተቀበልልኝ።
ምክንያቱም ይህ ሰው ሕዝባችንን ይወድዳል፤ ምኵራባችንንም ያሠራልን እርሱ ነው።”