አምላኬ ሆይ፤ ልብን እንደምትመረምርና ቅንነትን እንደምትወድድ ዐውቃለሁ፤ እኔም ይህን ሁሉ የሰጠሁት በበጎ ፈቃድና በቀና መንፈስ ነው። አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በበጎ ፈቃዱ እንዴት እንደ ሰጠ አይቻለሁ።
“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል።
እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው።
የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ሐሳብ ለዘላለም በሕዝብህ ልብ ጠብቀው፤ ልባቸውንም ለአንተ ታማኝ አድርገው።
ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ለእግዚአብሔር ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው።
በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አካሄዱ ክፈለው፤
አካሄዱ የቀና፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር፤
ልቤን መረመርኸው፣ በሌሊት ጠጋ ብለህ ፈተንኸኝ፤ ፈተሽኸኝ አንዳች አላገኘህብኝም፤ አንደበቴም ዕላፊ አልሄደም።
እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤ ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ።
ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤ ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው።
ልብንና ኵላሊትን የምትመረምር፣ ጻድቅ አምላክ ሆይ፤ የክፉዎችን ዐመፅ አጥፋ፤ ጻድቁን ግን አጽና።
እግዚአብሔር ልበ ጠማሞችን ይጸየፋል፤ በመንገዳቸው ነቀፋ በሌለባቸው ሰዎች ግን ደስ ይሰኛል።
ለሰው መንገዱ ሁሉ ንጹሕ መስሎ ይታየዋል፤ መነሻ ሐሳቡ ግን በእግዚአብሔር ይመዘናል።
ብር በማቅለጫ፣ ወርቅም በከውር፤ እግዚአብሔርም ልብን ይፈትናል።
ለሰው መንገዱ ሁሉ ቀና ይመስለዋል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል።
“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ፤ የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ።
ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ሁልጊዜ እጥራለሁ።
እንግዲህ ትምክሕታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋራ ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደ ኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው።
እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወድዳል።
አምላክህ እግዚአብሔር ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጕዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ።
በእናንተ በምታምኑት መካከል ሳለን እንዴት በቅድስና፣ በጽድቅ እንዲሁም ያለ ነቀፋ ሆነን እንደ ኖርን እናንተም እግዚአብሔርም ምስክሮች ናችሁ።
ወንድሜ ሆይ፤ በጌታ እንድትጠቅመኝ እፈልጋለሁ፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ።
ወንድሜ ሆይ፤ የቅዱሳንን ልብ ስላሳረፍህ ከፍቅርህ ታላቅ ደስታና መጽናናት አግኝቻለሁ።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።
ልጆቿንም በሞት እቀጣቸዋለሁ። ከዚያም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ ልብንና ሐሳብን የምመረምር መሆኔን ይረዳሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ።
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።