እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው።
አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረዥም ጊዜ በእንግድነት ኖረ።
“እኔ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ሆኜ በመካከላችሁ የምኖር ነኝና ለመቃብር የምትሆን ቦታ ሽጡልኝ፤ የሚስቴንም ሬሳ ልቅበርበት።”
እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ።”
ብዙ ሀብት ስለ ነበራቸው ዐብረው መኖር አልቻሉም፤ የነበሩበትም ስፍራ ከከብቶቻቸው ብዛት የተነሣ ሊበቃቸው አልቻለም።
ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍሁት ዘመን 130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋራ ሲነጻጸር ዐጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት።
“ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ቸርነት እናደርግ ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው?
እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው።
ሰው ግን ይሞታል፤ ክንዱንም ይንተራሳል፤ ነፍሱም ትወጣለች፤ ከእንግዲህስ የት ይገኛል?
እንደ አበባ ይፈካል፤ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላ ይፈጥናል፤ አይጸናምም።
እኛ ትናንት ስለ ተወለድን አንዳች አናውቅምና፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው።
ዘመኖቼ እንደ ምሽት ጥላ ናቸው፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ።
እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር።
ሰው እንደ እስትንፋስ ነው፤ ዘመኑም ፈጥኖ እንደሚያልፍ ጥላ ነው።
“እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴን አድምጥ፤ ልቅሶዬንም ቸል አትበል፤ በአንተ ፊት እኔ መጻተኛ ነኝና፤ እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝ።
ላለመመለስ ከመሰናበቴ በፊት፣ ዳግመኛ ደስ ይለኝ ዘንድ ዐይንህን ከላዬ አንሣ።”
ዘመናችን ሁሉ በቍጣህ ዐልፏልና፤ ዕድሜያችንንም በመቃተት እንጨርሳለን።
ሰው በሕይወት ሳለ፣ እንደ ጥላ በሚያልፉት ጥቂትና ከንቱ በሆኑት ቀኖቹ፣ ለሰው መልካም የሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? እርሱ ከሄደ በኋላስ ከፀሓይ በታች የሚሆነውን ማን ሊነግረው ይችላል?
“ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ።
ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድን ናት? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ።
ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ።