ደግሞም ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋራ ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም።
በዐሥራ አንደኛው ዓመት ቡል በተባለውም በስምንተኛው ወር ቤተ መቅደሱ በዝርዝር ጥናቱ መሠረት እንደ ታቀደው ተፈጸመ፤ ሠርቶ የጨረሰውም በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር።
እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጉንና ሥርዐቱን ተጠንቅቀህ ብትጠብቅ ይሳካልሃል፤ አይዞህ ጠንክር፤ በርታ፤ ተስፋም አትቍረጥ።
ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።”
“የእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የካህናቱ አለቃ አማርያ፣ የንጉሡ በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የይሁዳ ነገድ መሪ የሆነው የእስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑ ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ሆነው ያገለግላሉ፤ በርትታችሁ ሥሩ፤ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርጉ ጋራ ይሁን።”
ዕዝራ፣ ነገሩ በእጅህ ነው፤ ተነሥ! እኛም እንደግፍሃለን፤ በርትተህም አድርገው።”
እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና አትፍራ ይልሃል፤ እረዳሃለሁ።
ቀጥሎም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሐጌ፣ ይህን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝ” ይላል እግዚአብሔር።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤
ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?
ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ።
ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”
አምላክህ እግዚአብሔር መሓሪ አምላክ ነውና አይተውህም ወይም አያጠፋህም፤ ወይም ደግሞ ለአባቶችህ በመሐላ ያጸናላቸውን ቃል ኪዳን አይረሳም።
ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል።