እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጉንና ሥርዐቱን ተጠንቅቀህ ብትጠብቅ ይሳካልሃል፤ አይዞህ ጠንክር፤ በርታ፤ ተስፋም አትቍረጥ።
“እነሆ፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ እንግዲህ በርታ፤ ሰውም ሁን።
የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የምታደርገው ሁሉ እንዲከናወንልህ፣ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው በመንገዶቹ ተመላለስ፣ ሥርዐቶቹንና ትእዛዞቹን፣ ሕጎቹንና ደንቦቹን ጠብቅ፤
ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።”
ደግሞም ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋራ ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም።
አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምን ጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ።’
በምድሪቱ ሰላም ስለ ሰፈነ፣ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። እግዚአብሔር ዕረፍት ስለ ሰጠውም፣ በዘመኑ የተዋጋው ማንም አልነበረም።
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።
እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።
“በርቱ፤ ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋራ ያለው ከርሱ ጋራ ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና ዐብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም።
እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣ በዚያ ጊዜ አላፍርም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍትሕን ለንጉሥ፣ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ ዐድል፤
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል፣ በዚያ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ፣ ለመገንባት እጃችሁን አበርቱ።
ኢየሱስም፣ “ግድ የለም ፍቀድልኝ፤ ይህን በማድረግ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” አለው፤ ዮሐንስም በነገሩ ተስማማ።
ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት።
ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ።
አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።
በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ።
እንግዲህ ልጄ ሆይ፤ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ።
በመጽሐፍ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ ብትፈጽሙ፣ መልካም እያደረጋችሁ ነው።
በትእዛዝህ ላይ የሚያምፅና ለቃልህ የማይታዘዝ ሁሉ ይገደል፤ ብቻ አንተ ጽና፤ አይዞህ፤ በርታ።”