“አቤቱ፤ እግዚአብሔር እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።
ከግብጽ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ።
አምላክ ሆይ፤ በጆሯችን ሰምተናል፤ አባቶቻችን በቀድሞ ዘመን፣ እነርሱ በነበሩበት ዘመን፣ ያደረግኸውን ነግረውናል።
ጌታ ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋራ የሚወዳደር ሥራ የለም።
በላይ በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋራ ማን ሊስተካከል ይችላል? ከሰማያውያን ፍጥረታትስ መካከል ማን እግዚአብሔርን ይመስለዋል?
የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ታማኝነትህም ከብቦሃል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል ነህና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ያልህ ነህ።
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ?
እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጓልና።”
ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።
አለዚያ በአንተ በሹማምትህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው።
እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋራ ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋራ ታነጻጽሩታላችሁ?
ቅዱሱ፣ “ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።
“ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም።
“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
“እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።
እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔ በቀር አምላክ የለም። አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣ እኔ አበረታሃለሁ።
የከበረው ኀያል ክንድ፣ በሙሴ ቀኝ እጅ ላይ እንዲያርፍ አደረገ፤ ለራሱ የዘላለም ዝና እንዲሆንለት፣ ውሆችን በፊታቸው ከፈለ።
እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣
“ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን ለእኔ ለባሪያህ እነሆ ማሳየት ጀምረሃል፤ ለመሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር፣ አንተ የምታደርጋቸውን ሥራዎችና ታላላቅ ድርጊቶች መፈጸም የሚችል አምላክ ማነው?
“አንተን ለመርዳት በሰማያት ላይ፣ በደመናትም ላይ በግርማው እንደሚገሠግሥ፣ እንደ ይሹሩን አምላክ ያለ ማንም የለም።
እግዚአብሔር እርሱ አምላክ መሆኑን፣ ከርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ።
እንግዲህ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ አምላክ መሆኑን ዛሬ ዕወቅ፤ በልብህም ያዘው፤ ሌላም የለም።
“እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ ማንም የለም፤ ከአንተም በቀር ሌላ የለም፤ እንደ አምላካችን ያለ ዐለት የለም።