መዝሙር 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት ቅኔ። 1 አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ። 2 እግዚአብሔርን አልሁት፥ “አንተ ጌታዬ ነህ፤ በጎነቴን አትሻትምና። 3 ፈቃድህ ሁሉ በምድር ባሉት ቅዱሳን ላይ ተገለጠ። 4 ደዌያቸው በዛ፤ ከዚያም በኋላ ተፋጠኑ፤ በደም ማኅበራቸው አልተባበርም። ስማቸውንም በአፌ አልጠራም። 5 እግዚአብሔር የርስቴ ዕድል ፋንታና ጽዋዬ ነው፥ ርስቴን የምትመልስ አንተ ነህ። 6 ይይዙኝ ዘንድ ገመድ ጣሉብኝ፥ ርስቴ ግን ተያዘልኝ።” 7 እንዳስተውል ያደረገኝን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ ደግሞም በሌሊት ኵላሊቶች ይገሥጹኛል። 8 ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። 9 ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ምላሴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬ ደግሞ በተስፋው ያድራል፤ 10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። 11 የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘለዓለም ፍስሓ አለ። |