ዮሐንስ 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታችን ወደ አብ እንደ ጸለየ 1 ጌታችን ኢየሱስም ይህን ነገር ተናግሮ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አነሣና እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአልና ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ 2 ሥጋ በለበሰው ሁሉ ላይ ሥልጣንን እንደ ሰጠኸው መጠን ለሰጠኸው ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸው ዘንድ። 3 ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንህ አንተን፥ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት። 4 እኔ ልሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርሁህ። 5 አሁንም አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ። 6 “ከዓለም ለይተህ ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁ፤ ያንተ ነበሩ፤ እነርሱንም ለእኔ ሰጥተኸኛል፤ ቃልህንም ጠበቁ። 7 የሰጠኸኝም ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ ዛሬ ዐወቁ። 8 የሰጠኽኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀብለው ከአንተ እንደ ወጣሁ በእውነት ዐወቁ፤ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። 9 እኔ ስለ እነርሱ እለምናለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም አይደለም፤ ስለ ሰጠኸኝ ነው እንጂ፤ ያንተ ናቸውና። 10 የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተም የሆነ የእኔ ነው፤ እኔም በእነርሱ ከብሬአለሁ። 11 እንግዲህ በዓለም አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ይኖራሉ፤ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ በስምህ ጠብቃቸው፤ 12 እኔ በዓለም ከእነርሱ ጋር ሳለሁ ግን የሰጠኸኝን በስምህ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፉም ቃል ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳን አልጠፋም። 13 አሁን ግን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ደስታዬ ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን በዓለም እናገራለሁ። 14 እኔ ቃልህን ሰጠኋቸው፤ ዓለም ግን ጠላቸው፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱ ከዓለም አይደሉምና። 15 ከክፉ ነገር እንድትጠብቃቸው ነው እንጂ ከዓለም እንድትለያቸው አልለምንም። 16 እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና። 17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነውና። 18 አንተ እኔን ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም እነርሱን ወደ ዓለም ላክኋቸው። 19 እነርሱም በእውነት ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ስለ እነርሱ እኔ ራሴን እቀድሳለሁ። 20 “የምለምንህም ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም፤ በቃላቸው ስለሚያምኑብኝም ነው እንጂ፤ 21 ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተ አብ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም እንደ እኛ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ። 22 እኔም የሰጠኸኝን ክብር ሰጠኋቸው፤ እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም እንደ እኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ። 23 እኔ በእነርሱ እኖራለሁ፤ አንተም በእኔ፤ በአንድ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፤ አንተም እንደ ላክኸኝና እንደ ወደድኸኝ እኔም እነርሱን እንደ ወደድኋቸው። 24 አባት ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ እኔ ባለሁበት አብረውኝ ይኖሩ ዘንድና የሰጠኸኝን ክብሬን ያዩ ዘንድ እወድዳለሁ፤ ዓለም ሳይፈጠር ወድደኸኛልና። 25 ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን ዐወቅሁህ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ዐወቁ። 26 እኔን የወደድህበት ፍቅር በእነርሱ ይኖር ዘንድ፥ እኔም በእነርሱ እኖር ዘንድ ስምህን ነገርኋቸው፤ ደግሞም እነግራቸዋለሁ፤” |