ዮሐንስ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታችን ኢየሱስ እውነተኛ የወይን ሐረግ ስለ መሆኑ 1 “እውነተኛ የወይን ሐረግ እኔ ነኝ፤ ተካዩም አባቴ ነው። 2 በእኔ ያለውን፥ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍም ሁሉ ያስወግደዋል፤ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን በብዙ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3 እናንተ ግን ስለ ነገርኋችሁ ቃል ፈጽማችሁ ንጹሓን ናችሁ። 4 በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና። 6 በእኔ የማይኖር ቢኖር እንደ ደረቅ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጥሉታል፤ ሰብስበውም በእሳት ያቃጥሉታል። 7 በእኔም ብትኖሩ ቃሌም በእናንተ ቢኖር የምትሹትን ሁሉ ትለምናላችሁ፤ ይደረግላችሁማል። 8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩ፥ ደቀ መዛሙርቴም ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። 9 አብ እንደ ወደደኝ እንዲሁ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬም ኑሩ። 10 የምትወዱኝ ብትሆኑ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ፥ በፍቅሩም እንደምኖር እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11 ደስታዬ በእናንተ ይኖር ዘንድ፥ ደስታችሁም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ። 12 “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ እንድቷደዱ የእኔ ትእዛዝ ይህች ናት። 13 ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደ ሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም። 14 እናንተስ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ካደረጋችሁ ወዳጆች ናችሁ። 15 እንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ እናንተን ግን ወዳጆች እላችኋለሁ፤ በአባቴ ዘንድ የሰማሁትን ሁሉ ነግሬአችኋለሁና። 16 እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደለም፤ እንድትሄዱ፥ ፍሬም እንድታፈሩ፥ ፍሬአችሁም እንዲኖር፤ አብንም በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ሁሉን እንዲሰጣችሁ ሾምኋችሁ። 17 እርስ በርሳችሁም እንድቷደዱ ይህን አዝዣችኋለሁ። ዓለም የጌታን ተከታዮች እንደሚጠላ 18 “ዓለም ቢጠላችሁ አስቀድሞ እኔን እንደ ጠላ ዕወቁ። 19 እናንተስ ከዓለም ብትሆኑ ዓለም በወደዳችሁ ነበር፤ ዓለም ወገኖቹን ይወዳልና፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ ከዓለም አይደላችሁምና ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። 20 እኔ፦ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም ያልኋችሁን ቃሌን ዐስቡ፤ እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ቢሆንስ ቃላችሁንም በጠበቁ ነበር። 21 ነገር ግን ስለ ስሜ ይህን ሁሉ ያደርጉባችኋል፤ የላከኝን አያውቁትምና። 22 ባልመጣሁና ባልነገርኋቸውስ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። 23 እኔን የሚጠላ አባቴን ይጠላል። 24 ሌላ ያልሠራውን ሥራ በመካከላቸው ባልሠራ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል። 25 ነገር ግን በኦሪታቸው፦ በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ስለመሥረፁ 26 “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። 27 እናንተም ትመሰክራላችሁ፤ ከጥንት ጀምሮ ከእኔ ጋር ኑራችኋልና። |