ኤርምያስ 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ሕዝብ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ 1 በዚያ ዘመን ይላል እግዚአብሔር፤ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። ሂዱ፦ እስራኤልንም አታጥፉ።” 3 እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሃለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁህ። 4 የእስራኤል ድንግል ሆይ እንደ ገና እሠራሻለሁ፤ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ትወጫለሽ። 5 እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ተክሎችን ትተክሊአለሽ፤ የምትተክሉ ትከሉ፤ አመስግኑም፤ 6 በኤፍሬም ተራሮች ላይ የሚከራከሩ፦ ተነሡ፤ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጠሩባት ቀን ትመጣለችና።” 7 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “የያዕቆብ ቤት ሆይ! ደስ ይበላችሁ፤ በአሕዛብም አለቆች ላይ እልል በሉ፤ አውሩ፤ አመስግኑም፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ። 8 እነሆ፥ ከሰሜን ሀገር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ ለበዓለ ፋሲካ እሰበስባቸዋለሁ፤ ብዙ አሕዛብም ይወለዳሉ፤ ወደዚህም ይመለሳሉ። 9 እያለቀሱ ሄዱ፤ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስሄዳቸዋለሁ፤ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና።” 10 አሕዛብ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና፥ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። 11 እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል፤ ከበረቱበትም እጅ አድኖታል። 12 ይመጣሉ፤ በጽዮንም ተራራ ደስ ይላቸዋል፤ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ፥ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ሀገርም ይሰበሰባሉ፤ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይራቡም። 13 በዚያን ጊዜም ደናግሉ በዘፈን ደስ ይላቸዋል፤ ጐበዛዝቱና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ እኔም ልቅሶአቸውን ወደ ደስታ እመልሳለሁ፤ ከኀዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። 14 የካህናቱንም የሌዊን ልጆች ሰውነት ከፍ ከፍ አደርጋታለሁ፤ አረካታለሁ፤ ሕዝቤም ከበረከቴ ይጠግባል፥” ይላል እግዚአብሔር። 15 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የኀዘን፥ የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምፅሽን ከልቅሶ፥ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። 17 ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ። 18 “ኤፍሬም ሲጨነቅ መስማትን ሰማሁ፤ እንዲህም አለ፦ ቀጣኸኝ እኔም እንዳልቀና ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ። 19 ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፤ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም። 20 በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የተወደደ ልጅ ነው፤ ደስ የሚያሰኝም ሕፃን ነው፤ በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት፤ ርኅራኄም እራራለታለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። 21 “ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዐምዶችን ትከዪ፤ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ! ተመለሺ፤ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ እያለቀስሽ ተመለሺ። 22 አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሰው ወደ ድኅነት ይመጣል።” ለእስራኤል ሕዝብ የሚመጣው ሀብት 23 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ ሀገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክህ የሚል ነገርን እንደ ገና ይናገራሉ። 24 በይሁዳ ከተሞችና በሀገሩ ሁሉ ከገበሬዎችና መንጋን ይዘው ከሚዞሩ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኛሉ። 25 የተጠማችውን ነፍስ ሁሉ አርክቻለሁና፥ የተራበችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና። 26 ስለዚህ ነቃሁ፤ ተመለከትሁም፤ እንቅልፌም ጣፈጠኝ። 27 “በእስራኤል ቤትና በይሁዳ ቤት የሰው ዘርና የእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 28 እንዲህም ይሆናል፤ አፈርሳቸውና ክፉ አደርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፥ እንዲሁ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። 29 በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም፦ አባቶች ጮርቃ የወይን ፍሬ በሉ፤ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤ 30 ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ ጮርቃውን የወይን ፍሬ የሚበላም ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ። 31 “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 32 ከግብፅ ሀገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። 33 ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 34 እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።” 35 ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን፥ ጨረቃንና ከዋክብትንም በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 36 “ይህ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘለዓለም ይቀራል።” 37 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰማይ እጅግ ከፍ ቢል፥ የምድርም መሠረት ፈጽሞ ዝቅ ቢል በዚያ ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ፥ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እንቃለሁ ይላል እግዚአብሔር። 38 “ከአናምሄል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር። 39 መጠንዋ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፤ ወደ ጎዓትም ይዞራል። 40 የአስሬሞትም ሸለቆ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረስ በር ማዕዘን ድረስ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም፤ አይፈርስምም። |