ኤርምያስ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ ወደ እግዚእብሔር ያቀረበው እሮሮ 1 አቤቱ! ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኀጢአተኞች መንገድ ስለ ምን ይቀናል? በደልንስ የሚያደርጉ ሁሉ ስለ ምን ደስ ይላቸዋል? 2 አንተ ተክለሃቸዋል፤ ሥር ሰድደዋል፤ ወልደዋል አፍርተውማል፤ በአፋቸውም አንተ ቅርብ ነህ፤ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ። 3 አንተ ግን አቤቱ! ዐውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፤ ልቤንም በፊትህ ፈትነሃል፤ እንደ በጎች ለመታረድ ጐትተህ ለያቸው፤ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው። 4 በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት ምድሪቱ የምታለቅሰውና የዱሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና እንስሶችና ወፎችም ጠፍተዋል። 5 እግሮችህ ሮጠው ይደክማሉ፤ ፈረሶችን ለምን ታስጌጣለህ? በሰላምም ምድር ላይ ለምን ትታመናለህ? በዮርዳኖስስ ጩኸት ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? 6 ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር ክደውሃልና፥ ጮኸውም በስተኋላህ ተሰበሰቡ፤ በመልካምም ቢናገሩህ አትመናቸው። 7 ቤቴን ትችአለሁ፤ ርስቴንም ጥያለሁ፤ ነፍሴ የምትወድዳትንም በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ። 8 ርስቴ በዱር እንደ አለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋንም አንሥታብኛለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ። 9 ርስቴ እንደ ጅብ ጕድጓድ ናትን? ወይስ በዙሪያዋ የሚከቡአት የሽፍቶች ዋሻ ናትን? የምድር አራዊት ሁሉ ይበሉአት ዘንድ ተሰብስበው ይመጣሉ። 10 ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፤ እድል ፈንታዬንም አርክሰዋል፤ የምወድዳትንም እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገዋታል። 11 እርስዋም ለፍጹም ጥፋት ሆናለች፤ ስለ እኔም ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች፤ በልቡም የሚያኖራት የለም። 12 ወራዶች ወደ ዱር ሁሉ መጥተዋል፤ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። 13 ስንዴን ትዘራላችሁ፤ እሾህንም ታጭዳላችሁ፤ ዕጣችሁም ምንም አይጠቅማችሁም፤ ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ በአዝመራችሁ ታፍራላችሁ። 14 እግዚአብሔር ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጎረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ። 15 ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ ይቅር እላቸዋለሁ፥ ሁላቸውንም በርስታቸው፥ እያንዳንዳቸውንም በምድራቸው አኖራቸዋለሁ። 16 በበዓል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ ፈጽመው ቢማሩ፥ በዚያ ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ። 17 ባይመለሱ ግን ያን ሕዝብ እነቅለዋለሁ፤ አስወግደዋለሁ፤ አጠፋውማለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። |