ኤፌሶን 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ልጆችና ስለ ወላጆች 1 ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታችን ታዘዙ፤ ይህ የሚገባ ነውና። 2 በሕግም ተስፋ ያለው የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው፥ “አባትህንና እናትህን አክብር፤ 3 መልካም ይሆንልህ ዘንድ፥ በምድር ላይም ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ።” 4 እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በእግዚአብሔር ተግሣጽና ምክር አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው። ስለ አገልጋዮችና ስለ አሳዳሪዎቻቸው 5 አገልጋዮችም በሥጋችሁ ለሚገዙአችሁ ጌቶቻችሁ በፍርሀትና በመደንገጥ፥ በሰፊ ልብም ለክርስቶስ እንደምትገዙ ታዘዙ። 6 የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሮች እንጂ ለሰው ደስ እንደሚያሰኝ ለታይታ አይደለም። 7 ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደምትገዙ በፍጹም ሰውነታችሁ በፍቅርና በበጎ ፈቃድ ተገዙላቸው። 8 ጌታም ቢሆን፥ አገልጋይም ቢሆን መልካም ያደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንደሚያገኝ ታውቃላችሁና። 9 እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ቍጣችሁን እያበረዳችሁ፥ በደላቸውንም ይቅር እያላችሁ፥ ትክክለኛውን አድርጉላቸው፤ ፊት አይቶ የማያዳላ ጌታ በእነርሱና በእናንተ ላይ በሰማይ እንደ አለ ታውቃላችሁና። ሃይማኖትና ፍጹም ተጋድሎ 10 እንግዲህስ ወዲህ በእግዚአብሔርና በኀይሉ ጽናት በርቱ። 11 የሰይጣንን ተንኰል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ። 12 ሰልፋችሁ፦ ከጨለማ ገዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና። 13 ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ። 14 እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ፤ የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ። 15 የሰላም ወንጌል ኀይልንም ተጫምታችሁ ቁሙ። 16 ከዚህም ሁሉ ጋር የሚንበለበሉ የክፉን ፍላፃዎች ሁሉ ማጥፋት እንድትችሉ የእምነትን ጋሻ አንሡ። 17 የመዳንንም የራስ ቍር በራሳችሁ ላይ ጫኑ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ ያዙ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 18 በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁልጊዜ ትጉ፤ 19 ለእኔም፦ ቃልን እንዲሰጠኝ፥ አፌንም ከፍቼ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንድናገር ጸልዩልኝ። 20 ስለ ወንጌልም በእስራት መልእክተኛ የሆንሁ፦ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ጸልዩ። 21 እናንተም ዜናዬን እንድታውቁ የምንወደው ወንድማችን የታመነ የእግዚአብሔር አገልጋይ ቲኪቆስ የምሠራውን ሁሉ ያስረዳችኋል። 22 ዜናዬን ታውቁ ዘንድ፥ ልባችሁም ይጽናና ዘንድ፥ ስለዚህ ወደ እናንተ ላክሁት። 23 ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ከእምነት ጋር ሰላምና ፍቅር ለወንድሞቻችን ይሁን። 24 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለ መጥፋት ከሚወዱት ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን። አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲኪቆስ እጅ ወደ ኤፌሶን ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን። |