መክብብ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ በስንፍናም ካለ ታላቅ ክብር ይልቅ ትንሽ ጥበብ ትበልጣለች። 2 የጠቢብ ልብ በስተቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተግራው ነው። 3 ደግሞም ሰነፍ በልቡ ፈቃድና መንገድ በሚሄድ ጊዜ አእምሮ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ሰንፍና ነው። 4 ትዕግሥት ታላቁን ኀጢአት ያስተሰርያልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። 5 ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ ባለማወቅ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ 6 ሰነፍ በታላቅ ማዕርግ ላይ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። 7 አገልጋዮች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ፥ መኳንንትም እንደ አገልጋዮች በምድር ላይ በእግራቸው ሲሄዱ አየሁ። 8 ለባልንጀራው ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። 9 ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ ዕንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል። 10 ምሣሩ ከዛቢያው ቢወልቅ ሰውየው ፊቱን ወዲያና ወዲህ ይላል፤ ብዙ ኀይልም ያስፈልገዋል። ጥበብ ግን ለብርቱ ሰው ትርፉ ነው፤ 11 እባብ ቢነድፍ ባለ መድኀኒትም ባያድን ባለ መድኀኒቱ አይጠቀምም። 12 የጠቢብ ሰው የአፉ ቃል ሞገስ ናት፤ የሰነፍ ከንፈሮች ግን ራሱን ይውጡታል። 13 የአፉ ቃል መጀመሪያ ስንፍና ነው፥ የንግግሩም ፍጻሜ ክፉ ነው። 14 ሰነፍ ነገርን ያበዛል፤ ሰውም የሆነውንና ወደ ፊት የሚሆነውን አያውቅም፤ ከእርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ማን ይነግረዋል? 15 የሰነፍ ድካሙ ያሠቃየዋል፥ ወደ ከተማ መሄድን አያውቅምና። 16 ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ ሀገር ሆይ፥ ወዮልሽ! 17 ንጉሥሽ የጌታ ልጅ የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ለብርታት በጊዜ የሚበሉ፥ የማያፍሩም፥ አንቺ ሀገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ። 18 በሰዎች ስንፍናና ቦዘኔነት የቤት ጣራ ይዘብጣል፥ በእጆች ስንፍናም ቤት ያፈስሳል። 19 ሰነፎች ሰዎች እንጀራን ለሣቅ ያደርጉታል፥ የወይን ጠጅም ሕያዋንን ደስ ያሰኛል፥ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል። 20 የሰማይ ዎፍ ቃልህን ያወጣዋልና፥ ክንፍ ያለውም ነገርህን ያወራዋልና በልብህ ዐሳብ እንኳን ቢሆን ንጉሥን አትሳደብ፥ በመኝታ ቤትህም ባለጠጋን አትሳደብ። |