ዘዳግም 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ የሚያስከትለው መቅሠፍት 1 “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ከአንተ የበለጡትንና የበረቱትን አሕዛብ፥ የቅጽራቸው ግንብ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላላቆች ከተሞችን ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ዛሬ ዮርዳኖስን ትሻገረዋለህ። 2 አንተም የምታውቃቸው፥ ስለ እነርሱም፦ በዔናቅ ልጆች ፊት መቆም ማን ይችላል? ሲባል የሰማኸው ታላቅ፥ ብዙና ረዥም ሕዝብ የዔናቅ ልጆች ናቸው። 3 አምላክህም እግዚአብሔር በፊትህ እንዲያልፍ ዛሬ ዕወቅ፤ እርሱ የሚበላ እሳት ነው፤ እርሱ ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ያዋርዳቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ነገረህ ከፊትህ ያርቃቸዋል፥ ፈጥኖም ያጠፋቸዋል። 4 አምላክህ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ባወጣቸው ጊዜ፦ ስለ ጽድቄ እወርሳት ዘንድ ወደዚች መልካም ምድር እግዚአብሔር አገባኝ ብለህ በልብህ አትናገር፤ 5 ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኀጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው። 6 እንግዲህ አንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነህና አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር ርስት አድርጎ የሰጠህ ስለ ጽድቅህ እንዳይደለ ዛሬ ዕወቅ። 7 “አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ ምን ያህል እንዳሳዘንኸው፥ ከግብፅ ሀገር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ ስፍራ እስከ መጣችሁ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ አስብ፤ አትርሳም። 8 በኮሬብ ደግሞ እግዚአብሔርን አሳዘናችሁት፤ እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ በእናንተ ላይ ተቈጣ። 9 ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላት እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፤ ውኃም አልጠጣሁም። 10 እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉትን ሁለት የድንጋይ ጽላት ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁ ጊዜ እግዚአብሔር በተራራው ላይ የነገረኝ ቃል ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር። 11 ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊትም በኋላ እግዚአብሔር ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ የቃል ኪዳኑን ጽላት ሰጠኝ። 12 እግዚአብሔርም አለኝ፦ ተነሥተህ ከዚህ ፈጥነህ ውረድ፤ ከግብፅ ያወጣሃቸው ሕዝብህ በድለዋልና፤ ፈጥነው ካዘዝኋቸው መንገድ ፈቀቅ ብለዋልና፥ ቀልጦ የተሠራ ምስልም ለራሳቸው አድርገዋልና። 13 እግዚአብሔርም አለኝ፦ ‘አንድ ጊዜም ሁለት ጊዜም እንዲህ ብዬ ነገርሁህ፤ ይህ ሕዝብ አንገተ ደንዳና ሕዝብ እንደ ሆነ አይችአለሁ፤ 14 አጠፋቸው ዘንድ፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስስ ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ለሚበረታና እጅግ ለሚበዛ ሕዝብ አደርግሃለሁ።’ 15 እኔም ተመልሼ ከተራራው ወረድሁ፤ ተራራውም በእሳት ይነድድ ነበር፤ ሁለቱም የቃል ኪዳን ጽላት በሁለቱ እጆች ነበሩ። 16 እነሆ፥ በአምላካችሁ እግዚአብሔር ፊት እንደ በደላችሁ፥ ለእናንተም ቀልጦ የተሠራ ምስል ሠርታችሁ ልትጠብቁት እግዚአብሔር ካዘዛችሁ መንገድ ፈጥናችሁ ፈቀቅ እንዳላችሁ ባየሁ ጊዜ፥ 17 ሁለቱንም ጽላት ያዝሁ፤ ከሁለቱም እጆች ጣልኋቸው፤ በእናንተም ፊት ሰበርኋቸው። 18 ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቈጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዳግመኛ ለመንሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። 19 እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ ከተቈጣባችሁ ከቍጣውና ከመዓቱ የተነሣ ፈራሁ፤ እግዚአብሔርም በዚያን ጊዜ ደግሞ ሰማኝ። 20 እግዚአብሔርም አሮንን ሊያጠፋው እጅግ ተቈጣው፤ ስለ አሮንም ደግሞ በዚያን ጊዜ ጸለይሁ። 21 ስለ አደረጋችሁትም ኀጢአት የጥጃውን ምስል ወሰድሁ፤ በእሳትም አቃጠልሁት፤ አደቀቅሁትም፤ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨሁት፤ እንደ ትቢያም ሆነ፤ ትቢያውንም ከተራራው በሚወርድ ወንዝ ጨመርሁት። 22 “በውዕየት፥ በፈተናም በምኞት መቃብርም እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። 23 እግዚአብሔርም፦ ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፤ በእርሱም አላመናችሁም፤ ቃሉንም አልሰማችሁም። 24 ለእናንተ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዐመፀኞች ነበራችሁ። 25 “እግዚአብሔርም፦ ያጠፋችሁ ዘንድ ስለ ተናገረ ቀድሞ እንደ ለመንሁ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ለመንሁ። 26 በእግዚአብሔርም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ የአማልክት ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅ ኀይልህ የተቤዠሃቸውን፥ በጠነከረችውም እጅህና በተዘረጋች ክንድህ ከግብፅ ያወጣሃቸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። 27 በራስህ የማልህላቸውን አገልጋዮችህን አብርሃምንና ይስሐቅን፥ ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፥ ክፋቱንም፥ ኀጢአቱንም አትመልከት፤ 28 ከእርስዋ እኛን ያወጣህባት ምድር ሰዎች፦ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና፥ ጠልቶአቸውማልና ስለዚህ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው እንዳይሉ። 29 እነርሱም በታላቅ ኀይልህ፥ በጸናውና በተዘረጋውም ክንድህ ከግብፅ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው። |