ሐዋርያት ሥራ 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጳውሎስና ስለ አይሁድ ክርክር 1 አንፊጶልና አጶሎንያ ወደሚባሉ ሀገሮችም ሄዱ፤ የአይሁድ ምኵራብ ወደ አለበት ወደ ተሰሎንቄም ደረሱ። 2 ጳውሎስም እንደ አስለመደው ወደ እነርሱ ገብቶ ሦስት ሳምንት ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ሲከራከራቸው ሰነበተ። 3 ክርስቶስ እንዲሞት ከሙታንም ተለይቶ እንዲነሣ፥ እየተረጐመና እየአስተማራቸው፥ “ይህ እኔ የነገርኋችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” ይል ነበር። 4 ከእነርሱና ከደጋጎች አረማውያንም ብዙ ሰዎች፥ ከታላላቆች ሴቶችም ጥቂቶች ያይደሉ አምነው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ሆኑ። 5 የማያምኑ አይሁድ ግን ቀኑባቸው፤ ከገበያም ክፉዎች ሰዎችን አምጥተው፥ ሰዎችንም ሰብስበው ሀገሪቱን አወኳት፤ ፈለጓቸውም፤ የኢያሶንን ቤትም በረበሩ፤ ወደ ሕዝቡም ሊያወጧቸው ሽተው ነበር። 6 በአጧቸውም ጊዜ ኢያሶንን ጐተቱት፤ በዚያም የነበሩትን ጓደኞች ጭምር ወደ ሹሞቹ ወሰዱአቸው፤ እየጮኹም እንዲህ ይሉ ነበር፥ “ዓለምን የሚያውኳት እነዚህ ናቸው፤ ወደዚህም መጥተዋል። 7 ይህ ኢያሶንም ተቀበላቸው፤ እነርሱም በቄሣር ላይ የወንጀል ሥራ ይሠራሉ፤ ሌላ ሕግንም ያስተምራሉ፤ ኢየሱስም ሌላ ንጉሥ ነው” ይላሉ። 8 ሕዝቡና የከተማው ሹሞችም ይህን በሰሙ ጊዜ ታወኩ። 9 ከኢያሶንና ከጓደኞቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። 10 ወንድሞች ግን ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሸኙአቸው፤ ወደዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ። 11 በተሰሎንቄ ካሉትም እነርሱ ይሻላሉ፤ በፍጹም ደስታ ቃላቸውን ተቀብለዋልና፤ ነገሩም እንደ አስተማሩአቸው እንደ ሆነ ለመረዳት ዘወትር መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር። 12 ከመካከላቸውም ያመኑ ብዙዎች ነበሩ፤ ከአረማውያን ወገን የሆኑ ብዙ ደጋግ ሴቶችም ነበሩ፤ ወንዶችም ብዙዎች ነበሩ። 13 በተሰሎንቄ የነበሩ አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ አስተማረ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አወኩአቸው። 14 ያንጊዜም ወንድሞች ጳውሎስን ሸኝተው ወደ ባሕር አደረሱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን በዚያው ቀሩ። 15 ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴና ከተማ ድረስ አብረውት መጥተው ነበርና ፈጥነው ይከተሉት ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ላካቸው፤ ተመልሰውም ሄዱ። ስለ ጳውሎስ መታወክ 16 ጳውሎስም በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ከተማው ሁሉ ጣዖት ሲያመልኩ ባየ ጊዜ ልቡናው ተበሳጨ። 17 ስለዚህም በምኵራብ አይሁድንና እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ሁልጊዜም በገበያ የሚያገኛቸውን ሁሉ ይከራከራቸው ነበር። 18 የኤፌቆሮስን ትምህርት ከተማሩ ፈላስፋዎች መካከልና ረዋቅያውያን ከሚባሉት ወገን የሆኑ ሌሎች ፈላስፎችም የተከራከሩት ነበሩ፤ እኩሌቶችም፥ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎችም፥ “ስለ ኢየሱስ ከሙታን ስለ መነሣቱም ሰብኮላቸዋልና የአዲስ አምላክ ትምህርትን ያስተምራል” አሉ። 19 ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደሚባል ሸንጎ ወሰዱት፤ እንዲህም አሉት፥ “ይህን የምታስተምረውን አዲስ ትምህርት እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? እስቲ ንገረን? 20 በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና እኛም ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ልንረዳ እንወዳለን።” 21 የአቴና ሰዎችና በዚያም የነበሩ እንግዶች ሁሉ አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር ሌላ ዐሳብ አልነበራቸውም። ጳውሎስ በፍርድ ሸንጎ ውስጥ ስለ አደረገው ንግግር 22 ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ ውስጥ ቆሞ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የአቴና ሰዎች! በሥራችሁ ሁሉ አማልክትን ማምለክ እንደምታበዙ አያችኋለሁ። 23 በዚህም ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን የምታመልኩበትን መሠዊያችሁን አየሁ፤ እነሆ፥ እኔ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ። 24 ዓለሙንና በእርሱም ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። 25 እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌላውንም ነገር ሁሉ ለሁሉ ይሰጣልና እንደ ችግረኛ የሰው እጅ አያገለግለውም። 26 እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው። 27 ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉት ዘንድ፤ ነገር ግን ከሁላችን የራቀ አይደለም። 28 እኛ በእርሱ ሕይወትን እናገኛለን፤ በእርሱም እንንቀሳቀሳለን፤ በእርሱም ጸንተን እንኖራለን፤ ከመካከላችሁም፦ ‘እኛ ዘመዶቹ ነን’ የሚሉ ፈላስፎች አሉ። 29 እንግዲህ እኛ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆን በሰው ዕውቀትና ብልሀት በተቀረጸ በድንጋይና በብር፥ በወርቅም አምላክነቱን ልንመስለው አይገባም። 30 የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፤ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሓ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዞአል። 31 በመረጠው ሰው እጅ በዓለም በእውነት የሚፈርድባትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱን ከሙታን ለይቶ በማስነሣቱም ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት መልሶአልና።” 32 የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ ሌሎችም፥ “ስለዚህ ነገር በሌላ ቀን እናዳምጥሃለን” አሉት። 33 ጳውሎስም ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ። 34 አምነው የተከተሉት ሰዎችም ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ከአርዮስፋጎስ ባለሥልጣኖች ወገን የሚሆን ዲዮናስዮስ ነበር፤ ደማሪስ የምትባል ሴትም ነበረች፤ ሌሎችም አብረዋቸው ነበሩ። |