2 ቆሮንቶስ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የመቄዶንያ ቤተ ክርስቲያን አስተዋፅኦ 1 ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እነግራችኋለሁ። 2 በብዙ መከራ ከመፈተናቸው የተነሣ ደስታቸው በዝቶአልና፤ በድህነታቸው ጥልቅነትም የለጋስነታቸው ባለጠግነት በዝታለችና። 3 እነርሱ ሲቻላቸው፥ ሳይቻላቸውም እንስጥ በማለት ቈራጦች ለመሆናቸው ምስክራቸው እኔ ነኝና። 4 ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት መላልሰው ማለዱን። 5 እነርሱ አስቀድመው በፈቃዳቸው፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔርም፥ ለእኛም አሳልፈው ሰጥተዋልና እኛ እንደ አሰብነው አይደለም፤ 6 ይህንም የቸርነት ሥራ እንደ ጀመረ ይፈጽምላችሁ ዘንድ ቲቶን ማለድነው። 7 በሁሉ ነገር በእምነትና በቃል፥ በዕውቀትም፥ በትጋትም በእናንተ ዘንድ በሆነው ሁሉ እኛን በመውደዳችሁ ፍጹማን እንደ ሆናችሁ፥ እንዲሁም ደግሞ ይህቺን ስጦታ አብዙ። 8 በግድ የምላችሁ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ለዚህ ሥራ የሚተጉለት አሉና የፍቅራችሁን እውነተኛነት አሁን መርምሬ ተረዳሁ። 9 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለ እናንተ ራሱን ድሃ አደረገ። 10 በዚህም የሚጠቅማችሁን እመክራችኋለሁ፤ ይህን ከማድረጋችሁ በፊት ፈቅዳችኋልና፤ ከአምና ጀምሮም ይህን ጀምራችኋል። 11 አሁንም አድርጉ፤ ፈጽሙም፤ መፍቀድ ከመሻት ነውና፤ ማድረግም ከማግኘት ነውና። 12 ፈቃድ ካለም፥ ሰው በሚቻለው መጠን ቢሰጥ ይመሰገናል፤ በማይቻለውም መጠን አይደለም። 13 በዚህ ወራት ተካክላችሁ እንድትኖሩ ነው እንጂ ሌላው እንዲያርፍ እናንተን የምናስጨንቅ አይደለም። 14 ኑሮአችሁ በሁሉ የተካከለ ይሆን ዘንድ፥ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጕድለት ይመላልና፥ የእነርሱም ትርፍ የእናንተን ጕድለት ይመላልና። 15 መጽሐፍ እንዳለ፥ “ብዙ ያለው አላተረፈም፤ ጥቂት ያለውም አላጐደለም።” ስለ ቲቶና ጓደኞቹ 16 በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያን መትጋት የሰጠ እግዚአብሔር የተመሰገነ ነው። 17 ልመናችንንም ተቀብሎ፥ ጨክኖ ወደ እናንተ ይመጣ ዘንድ ቸኵሏል። 18 ስለ ወንጌል ትምህርት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ያመሰገኑትን ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ልከናል። 19 ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግልባት በዚች ጸጋ ከእኛ ጋር አንድ ይሆን ዘንድ በአብያተ ክርስቲያናት ተሾመ። 20 ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን። 21 በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ፥ ነገር ግን በሰው ፊትም መልካሙን ነገር እናስባለንና። 22 በብዙ የፈተንነውንና በሁሉም ነገር ትጉህ ሆኖ ያገኘነውን አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን። 23 ቲቶም ቢሆን፥ ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ጓደኛዬ ነው፥ ወንድሞቻችንም ቢሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ክብር የአብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያት ናቸው። 24 አሁንም መዋደዳችሁንና እኛም በእናንተ የምንመካበትን ሥራ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት በግልጥ አሳዩአቸው። |