1 ቆሮንቶስ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ፍቅር 1 የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፥ የመላእክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮህ ነሐስ፥ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው። 2 ትንቢት ብናገር፥ የተሰውረውን ሁሉ፥ ጥበብንም ሁሉ ባውቅ፥ ተራራ እስከ ማፍለስ የሚያደርስ ፍጹም እምነትም ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3 ገንዘቤን ሁሉ ለምጽዋት ብሰጥ፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል ብሰጥ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 4 ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ያስተዛዝናል፤ ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም። 5 ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም፤ ክፉ ነገርንም አያሳስብም። 6 ጽድቅን በመሥራት ደስ ያሰኛል እንጂ፥ ግፍን በመሥራት ደስ አያሰኝም። 7 በሁሉ ያቻችላል፤ በሁሉም ያስተማምናል፤ በሁሉም ተስፋ ያስደርጋል፥ በሁሉም ያስታግሣል። 8 ፍቅር ለዘወትር አይጥልም፤ ትንቢት የሚናገርም ያልፋል፤ ይሻራልም፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገርም ያልፋል፤ ይቀራል፤ የሚራቀቅም ያልፋል፤ ይጠፋል። 9 በየገጹ ጥቂት ጥቂት እናውቃለንና፤ ጥቂት ጥቂት ትንቢትም እንናገራለንና። 10 ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ያ ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። 11 እኔ ልጅ በነበርሁ ጊዜ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም እመክር ነበር፤ በአደግሁ ጊዜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሁሉ ሻርሁ። 12 አሁን ግን ታወቀኝ፤ በግልጥም ተረዳኝ፤ በመስታወትም እንደሚያይ ሰው ዛሬ በድንግዝግዝታ እናያለን፤ ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ አሁን በከፊል፥ ኋላ ግን እንደ ተገለጠልኝ መጠን ሁሉን አውቃለሁ። 13 አሁንም እነዚህ ሦስቱ እምነት፥ ተስፋና ፍቅር ጸንተው ይኖራሉ፤ ከሁሉ ግን ፍቅር ይበልጣል። |