Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 51 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ይቅርታን ለመለመን የቀረበ ጸሎት

1 አምላክ ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ይቅር በለኝ፤ ስለ ታላቁ ምሕረትህም ኃጢአቴን ደምስስልኝ።

2 በደሌን ሁሉ አጥበህ አስወግድልኝ፤ ከኃጢአቴም አንጻኝ።

3 እኔ ስሕተቴን ዐውቃለሁ፤ የኃጢአቴንም ብዛት ዘወትር እገነዘባለሁ።

4 እኔ ያመፅኩት በአንተ ላይ ነው፤ የበደልኩትም አንተን ብቻ ነው፤ አንተ የምትጠላውን ነገር አደረግሁ፤ ስለዚህ በእኔ ላይ መፍረድህና እኔንም መቅጣትህ ትክክል ነው።

5 ከተፀነስኩበት ጊዜ ጀምሮ ኀጢአተኛ ነኝ፤ ከተወለድኩበትም ጊዜ ጀምሮ በደለኛ ነኝ።

6 አንተ ቅንነትንና እውነትን ስለምትወድ የጥበብህን ምሥጢር አስተምረኝ።

7 በሂሶጵ ቅጠል ረጭተህ ኃጢአቴን አስወግድልኝ፤ እኔም እነጻለሁ። እጠበኝ፤ እኔም ከበረዶ ይበልጥ ነጭ እሆናለሁ።

8 የሰበርካቸውን አጥንቶቼን አድሰህ የደስታንና የሐሤትን ድምፅ አሰማኝ፤

9 ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፤ በደሌን ሁሉ ደምስስ።

10 አምላክ ሆይ! ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፤ አዲስና የጸና መንፈስን ስጠኝ።

11 ከፊትህ አታርቀኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድብኝ።

12 በአዳንኸኝ ጊዜ እንደ ሰጠኸኝ ዐይነቱን ደስታ ስጠኝ፤ ታዛዥ እንድሆን አድርገኝ

13 ከዚህ በኋላ ትእዛዝህን ለሕግ ተላላፊዎች አስተምራለሁ፤ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።

14 አቤቱ አዳኜ አምላኬ ሆይ! ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ ስለ አዳኝነትህም የምስጋና መዝሙር እዘምራለሁ።

15 እግዚአብሔር ሆይ! እንድናገር እርዳኝ፤ እኔም አመሰግንሃለሁ።

16 መሥዋዕት አያስደስትህም እንጂ ባቀረብኩልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም አያስደስትህም።

17 ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት የተሰበረ ልብ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።

18 አምላክ ሆይ! ጽዮንን ለመርዳት፥ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመገንባት እባክህ ፈቃድህ ይሁን።

19 በዚያን ጊዜ በትክክለኛ መሥዋዕትና በሚቃጠል መሥዋዕት ትደሰታለህ፤ እኛም በመሠዊያህ ላይ እንደገና ኰርማዎችን እናቀርባለን።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች