መዝሙር 41 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሕመም ጊዜ ጸሎት 1 ድኾችን የሚረዱ የተባረኩ ናቸው፤ እነርሱም በተቸገሩ ጊዜ እግዚአብሔር ይረዳቸዋል። 2 እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፤ በሕይወትም ያኖራቸዋል፤ በምድር ላይ ይባርካቸዋል፤ ለጠላቶቻቸውም አሳልፎ አይሰጣቸውም። 3 ታመውም በተኙበት አልጋ ላይ እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፤ ጤንነታቸውንም ይመልስላቸዋል። 4 እኔም “እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ስለ በደልኩ ምሕረትን አድርግልኝ፤ ከሕመም ፈውሰኝ” አልኩ። 5 ጠላቶቼ ብዙ ክፉ ነገር በእኔ ላይ በመናገር “መቼ ይሞታል? መቼስ ስሙ ተረስቶ ይቀራል?” ይላሉ። 6 እኔን ለመጐብኘት የሚመጡት ከልባቸው አይደለም፤ በእኔ ላይ መጥፎ ወሬ ይሰበስባሉ፤ በየቦታውም እየዞሩ ስሜን ያጠፋሉ። 7 የሚጠሉኝ ሁሉ በእኔ ላይ በሹክሹክታ ይናገራሉ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስብኝም ያቅዳሉ። 8 “ጽኑ ደዌ አድሮበት ለመሞት ተቃርቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከተኛበት አልጋ አይነሣም” ይላሉ። 9 እንጀራዬን ከእኔ ጋር አብሮ የበላ ከልብ የምተማመንበት ወዳጄ እንኳ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሥቶአል። 10 እግዚአብሔር ሆይ! ማረኝ፤ በጠላቶቼም ላይ ብድሬን እመልስ ዘንድ ጤንነቴንም መልስልኝ፤ 11 እኔን ድል በማድረጋቸው እንደ ተደሰቱ አይቀሩም፤ አንተም በእኔ ደስ እንደ ተሰኘህ ዐውቃለሁ። 12 ስለ ቅንነቴ እኔን ትረዳኛለህ፤ በፊትህም ለዘለዓለም ታኖረኛለህ። 13 ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! አሜን! አሜን! |