መዝሙር 32 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኃጢአትን ተናዝዞ ይቅርታ መቀበል 1 ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸውና በደላቸውም የተሰረየላቸው ሰዎች የተባረኩ ናቸው። 2 እግዚአብሔር ኃጢአቱን የማይቈጥርበት ከሽንገላም የራቀ ሰው የተባረከ ነው። 3 ኃጢአቴን ሳልናዘዝ በቀረሁ ጊዜ ቀኑን ሙሉ በመቃተቴ መላ ሰውነቴ ደከመ። 4 ቀንና ሌሊት በብርቱ ቀጣኸኝ፤ ርጥበት ያለው ነገር በበጋ ሙቀት እንደሚደርቅ ጒልበቴ በፍጹም አለቀ። 5 በዚያን ጊዜ ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ በደሌንም ከአንተ አልሰወርኩም፤ ኃጢአቴን ሁሉ ለአንተ ለመናዘዝ ወሰንኩ፤ አንተም ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር አልክልኝ። 6 ስለዚህ በጭንቀት ሰዓት እያንዳንዱ ለአንተ ታማኝ ሰው ወደ አንተ ይጸልይ፤ ብርቱ የመከራ ጐርፍ በሚመጣበት ጊዜ እርሱን አይነካውም። 7 አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ከመከራ ትጠብቀኛለህ፤ ስላዳንከኝ በከፍተኛ ድምፅ በደስታ እዘምራለሁ። 8 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ “አስተምርሃለሁ፤ የምትሄድበትንም መንገድ አሳይሃለሁ፤ ምክር እሰጥሃለሁ፤ እጠብቅሃለሁ።” 9 እንዲገቱ ለማድረግ በልባብና በልጓም እንደሚመሩት እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ የማይገባችሁ አትሁኑ። እንደዚያ ካላደረጋችሁ ፈረስና በቅሎ ወደ እናንተ አይቀርቡም። 10 የኃጢአተኞች መከራ ብዙ ነው። በእግዚአብሔር የሚታመኑትን ግን በዘለዓለማዊ ፍቅሩ ይሸፍናቸዋል። 11 ጻድቃን ሆይ! በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ፤ ልበ ቅኖች ሆይ! እልል በሉ! |