መዝሙር 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምክፍል አንድ ( መዝ. 1—41 ) የደግ ሰውና የክፉ ሰው አካሄድ 1 በክፉ ሰዎች ምክር የማይሄድ፥ የኃጢአተኞችን መንገድ የማይከተል፥ ከፌዘኞች ጋር ኅብረት የማያደርግ የተባረከ ነው። 2 እንዲህ ያለው ሰው፥ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፤ ቀንና ሌሊትም ያሰላስለዋል። 3 እርሱም፦ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፥ ቅጠሏም እንደማይረግፍ፥ በፈሳሽ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሥራ ሁሉ ይሳካለታል። 4 ክፉዎች ግን እንደዚህ አይደሉም፤ እነርሱ ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ገለባ ናቸው። 5 ስለዚህ ክፉ ሰዎች በፍርድ ቀን ከፍርድ አይድኑም፤ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ጉባኤ አይገኙም። 6 ስለዚህ እግዚአብሔር የጻድቃንን አካሄድ ያውቃል፤ የክፉ ሰዎች አካሄድ ግን የሚያመራው ወደ ጥፋት ነው። |