ዘኍል 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሞአባውያን እስራኤላውያንን ማሳታቸው 1 የእስራኤል ሕዝብ በሺጢም ሸለቆ ሰፍሮ በነበረበት ጊዜ ወንዶቹ እዚያ ከነበሩበት ሞአባውያን ሴቶች ጋር አመነዘሩ፤ 2 እነዚያም ሴቶች ለሞአብ ጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት እንዲመገቡ ጋበዙአቸው፤ እስራኤላውያንም የመሥዋዕቱን ምግብ በልተው ፔዖር በሚባለው ተራራ ላይ ለሚገኘው በዓል ለተባለውም ጣዖት ሰገዱ፤ 3 በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን በፔዖር ለባዓል ጣዖት በመስገዳቸው እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጣ። 4 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእስራኤል ላይ የነደደው ቊጣዬ ይበርድ ዘንድ የእስራኤልን መሪዎች ሁሉ ወስደህ በጠራራ ፀሐይ በሕዝብ ፊት ግደላቸው።” 5 ሙሴም ለእስራኤል መሪዎች “እያንዳንዳችሁ ከየነገዳችሁ በዓል ለሚባለው የፒዖር ጣዖት የሰገደውን ሰው ሁሉ ግደሉ” ብሎ ትእዛዝ አስተላለፈ። 6 ሙሴና መላው ማኅበር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተገኝተው በሚያለቅሱበት ጊዜ ከእስራኤላውያን አንዱ አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ በእነርሱ ፊት በማለፍ ወደ ቤተሰቡ አቀረባት። 7 የካህኑ የአሮን የልጅ ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ይህን ባየ ጊዜ ከተቀመጠበት በመነሣት ከጉባኤው መካከል ወጥቶ ሄደ፤ ጦርም አንሥቶ፥ 8 ሰውየውና ሴቲቱ ወዳሉበት ድንኳን ገባ፤ ሁለቱንም በአንድነት በጦር ወግቶ ገደላቸው፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያንን በማጥፋት ላይ የነበረው መቅሠፍት ቆመ፤ 9 ነገር ግን እስከዚያው ሰዓት ድረስ ያ መቅሠፍት ኻያ አራት ሺህ ሕዝብ አጥፍቶ ነበር። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11 “የካህኑ የአሮን የልጅ ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባደረገው ነገር ምክንያት በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያለኝ ቊጣ በርዶአል፤ ፊንሐስ ከእኔ በቀር ለሌላ አምላክ የሚሰግዱትን መታገሥ አልፈለገም፤ በቊጣዬ እስራኤልን ያላጠፋሁትም እርሱ ስለ እኔ ባሳየው ቅናት ነው። 12 ስለዚህ እኔ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር የሰላም ቃል ኪዳኔን የምሰጠው መሆኔን ንገረው። 13 እርሱ ለእኔ ለአምላኩ ቀናተኛ በመሆኑና የሕዝቡንም ኃጢአት በማስተስረዩ እርሱና ዘሮቹ በሙሉ ለዘለዓለም ካህናት ይሆናሉ።” 14 ከምድያማዊቱ ሴት ጋር የተገደለው እስራኤላዊ ስም የሳሉ ልጅ ዚምሪ ሲሆን እርሱም በስምዖን ነገድ ውስጥ የጐሣ አለቃ ነበር። 15 የሴቲቱም ስም ኮዝቢ ይባል ነበር፤ “ጹር” ተብሎ የሚጠራው አባትዋም በአንድነት የሚኖሩ የጥቂት ምድያማውያን ጐሣዎች አለቃ ነበር። 16 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17 “በምድያማውያን ላይ አደጋ ጥላችሁ ደምስሱአቸው፤ 18 ይህንንም የምታደርጉት እናንተን በፔዖር በማታለል ግፍ ስለ ሠሩባችሁና በፔዖር በወረደው መቅሠፍት ምክንያት በተገደለችው በአለቃቸው ልጅ በኮዝቢ አማካይነት በፈጸሙት ሽንገላ ነው።” |