Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ዮሐንስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ክርስቶስ ጠበቃችን መሆኑ

1 ልጆቼ ሆይ! ይህን የምጽፍላችሁ ኃጢአት እንዳትሠሩ ብዬ ነው። ነገር ግን ማንም ሰው ኃጢአት ቢሠራ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2 እርሱም ኃጢአታችንን ይደመስሳል፤ የእኛ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን የዓለሙም ሁሉ ኃጢአት የሚደመሰሰው በእርሱ ነው።

3 የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምንፈጽም ከሆንን እርሱን የምናውቅ መሆናችንን በዚህ እናረጋግጣለን።

4 “እግዚአብሔርን ዐውቀዋለሁ” እያለ የእርሱን ትእዛዞች የማይፈጽም ቢኖር ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።

5 ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቃል የሚታዘዝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር ፍጹም ነው፤ በእውነት በእርሱ የምንኖር መሆናችንም የሚታወቀው በዚሁ ነው፤

6 በእግዚአብሔር እኖራለሁ የሚል ሰው ክርስቶስ እንደ ኖረው መኖር አለበት።


አዲሱ ትእዛዝ

7 ወዳጆቼ ሆይ! ይህ የምጽፍላችሁ ትእዛዝ ከመጀመሪያው አንሥቶ የነበራችሁና የዱሮ ትእዛዝ ነው እንጂ አዲስ አይደለም፤ ይህም የዱሮ ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው።

8 ይሁን እንጂ በክርስቶስና በእናንተ ሕይወት ዘንድ እውነት ሆኖ የታየውን አዲስ ትእዛዝ እጽፍላችኋለሁ፤ ጨለማው ተወግዶ እውነተኛው ብርሃን አሁንም እያበራ ነው።

9 በብርሃን እኖራለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ገና በጨለማ ውስጥ ነው።

10 ወንድሙን የሚወድ ሁሉ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ሰውን የሚያሰናክል ነገር አይኖርም።

11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ይኖራል፤ በጨለማም ይመላለሳል፤ ጨለማውም ዐይኑን ስላሳወረው የሚሄድበትን አያውቅም።

12 ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአታችሁ በኢየሱስ ስም ይቅር ስለ ተባለላችሁ እጽፍላችኋለሁ።

13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን ስላወቃችሁት እጽፍላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ሰይጣንን ስላሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።

14 ልጆች ሆይ፥ አብን ስላወቃችሁት ጽፌላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያው የነበረውን ስላወቃችሁት ጽፌላችኃለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁና የእግዚአብሔር ቃል በልባችሁ ስለሚኖር፥ ሰይጣንንም ስላሸነፋችሁ ጽፌላችኋለሁ።

15 ዓለምን ወይም የዓለምን ነገር ሁሉ አትውደዱ። ዓለምን የሚወድ እግዚአብሔር አብን አይወድም።

16 በዓለም ያለው ሁሉ የሥጋ ምኞት፥ የዐይን አምሮት፥ የኑሮ ትምክሕት ከዓለም ነው እንጂ ከእግዚአብሔር አብ አይደለም።

17 ዓለምና ምኞቱም ያልፋሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘለዓለም ይኖራል።


የክርስቶስ ተቃዋሚ ከሆነው መጠንቀቅ

18 ልጆቼ ሆይ! ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ “የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል” ሲባል ሰምታችኋል፤ እነሆ፥ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ በዚህ ምክንያት የመጨረሻው ሰዓት መሆኑን እናውቃለን።

19 እነርሱ የወጡት ከእኛ መካከል ነው። ይሁን እንጂ ዱሮውንም ከእኛ ወገን አልነበሩም። ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋርም ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን አለመሆናቸው እንዲታወቅ ከእኛ መካከል ተለይተው ወጥተዋል።

20 እናንተ ግን ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ቀብቶአችኋል። ስለዚህ ሁላችሁም ሁሉን ነገር ታውቃላችሁ።

21 ለእናንተ የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፤ እናንተስ እውነትን ታውቃላችሁ፤ በእውነትም ሐሰት እንደማይገኝ ታውቃላችሁ።

22 እንግዲህ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማን ነው? እርሱ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው፤ አብንና ወልድንም ይክዳል።

23 ወልድን የሚክድ አብን አይቀበልም፤ በወልድ የሚያምን በአብ ያምናል።

24 ከመጀመሪያው ጀምሮ የሰማችሁት በልባችሁ ጸንቶ ይኑር፤ እናንተ ግን ከመጀመሪያው የሰማችሁት ቃል በልባችሁ ጸንቶ ከኖረ ከወልድና ከአብ ጋር አንድነት ይኖራችኋል።

25 ይህም ክርስቶስ የሰጠን ተስፋ የዘለዓለም ሕይወት ነው።

26 ስለሚያታልሉአችሁ ሰዎች ይህን ጻፍኩላችሁ፤

27 ከክርስቶስ የተቀበላችሁት መንፈስ በውስጣችሁ ስለሚኖር ሌላ አስተማሪ አያስፈልጋችሁም፤ እርሱ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ የሚያስተምራችሁም እውነትን ነው እንጂ ሐሰትን አይደለም። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራችሁ በክርስቶስ ኑሩ።

28 እንግዲህ ልጆቼ ሆይ! እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ ሳንፈራ በድፍረት እንድናየውና በሚመጣበት ቀን በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ፤

29 እርሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ መሆኑን ዕወቁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች