Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሕዝቅኤል 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጣኦት አምላኪዋ መገደል

1 በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ፥ እንዲህም አለ፦ እያንዳንዳቸው በእጃቸው የጦር ይያዙ፤ ከተማይቱን የሚቀጡ በዚህ ይምጡ።

2 እነሆ ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፥ እያንዳንዱም አጥፊውን መሣሪያ በእጁ ይዞ ነበር፥ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ፥ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።

3 የእስራኤልም አምላክ ክብር በላዩ ላይ አርፎ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መግቢያ ሄዶ ነበር፥ በፍታ የለበሰውን በወገቡም የጸሐፊ ቀለም ቀንድ የያዘውን ሰው ጠራ።

4 ጌታም እንዲህ አለው፦ በከተማይቱ መካከል፥ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኩሰት ሁሉ በሚተክዙና በሚያለቅሱ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክትን አድርግ።

5 እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ፦ እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፥ ዓይናችሁ አይራራ፥ አትዘኑም፤

6 ሽማግሌ፥ ወጣት፥ ድንግል፥ ሕፃናትንና ሴቶችን ግደሉ፥ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፥ በመቅደሴም ጀምሩ። በቤቱ ፊት ለፊት ከነበሩት ሽማግሌዎች ጀመሩ።

7 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ ቤቱን አርክሱ፥ አደባባዮቹንም በተገደሉት ሰዎች ሙሉ፥ ውጡ፤ እነርሱም ወጡ በከተማይቱም ውስጥ ገደሉ።

8 እነርሱ ሲገድሉ እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ ጮኽሁ፥ እንዲህም አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ትሩፍ ሁሉ ታጠፋለህን?

9 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ኃጢአት እጅግ በዝቶአል፥ ምድሪቱ በደም ተሞልታለች፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፥ ጌታ ምድሪቱን ትቶአታል፥ ጌታ አያይም ብለዋልና።

10 እኔም ደግሞ ዓይኔ አይራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ።

11 እነሆም በፍታ የለበሰው፥ የቀለም ቀንድም በወገቡ የያዘው ሰው፦ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ ብሎ በቃሉ መለሰ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች