Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ዜና መዋዕል 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


አብያ በይሁዳ ላይ መንገሡ

1 ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ።

2 ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበረ።

3 አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ተዋጊዎች ይዞ ወደ ጦርነት ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ።

4 አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤

5 የእስራኤል አምላክ ጌታ በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ የጨው ቃል ኪዳን ለዘለዓለም እንደሰጠ በውኑ አታውቁምን?

6 የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባርያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዓመፀ።

7 ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት።

8 “እንግዲህ አሁን እናንተ እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁና፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸውና በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የጌታን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ።

9 የአሮንን ልጆች የጌታን ካህናትና ሌዋውያንን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ለራሳችሁ ካህናትን አልሾማችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ለመቀደስ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል።

10 ለእኛ ግን አምላካችን ጌታ ነው፥ አልተውነውም፤ የጌታም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው።

11 በየጥዋቱና በየማታውም ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መዓዛው ያማረ ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የተቀደሰውንም ኅብስት በንጹሕ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የጌታን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል።

12 እነሆም፥ ጌታ በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ የጦርነት ማስጠንቀቅያ ድምፅ ያሰማሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ! አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከጌታ ጋር አትዋጉ።”

13 ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ለፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ ግን በስተ ኋላቸው ነበረ።

14 ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጦርነቱ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ ጌታም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ።

15 የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ ጌታ ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው።

16 የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ ጌታም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።

17 አብያና ሕዝቡ በታላቅ ውግያ ድል አደረጓቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ።

18 በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በጌታ ታምነው ነበርና አሸነፉ።

19 አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ።

20 ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ ጌታም ቀሰፈው፥ ሞተም።

21 አብያም ጸና፥ ዐሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆች ወለደ።

22 የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች