1 ዜና መዋዕል 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሮቤል ትውልድ 1 የእስራኤልም በኩር የሮቤል ልጆች እነዚህ ናቸው። እርሱ የበኩር ልጅ ነበረ፤ ነገር ግን የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኩርናው ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጠ፤ ትውልዱ ግን ከብኩርናው ጋር አልተቈጠረም። 2 ይሁዳም በወንድሞቹ መካከል በረታ፥ አለቃም ከእርሱ ሆነ፤ ብኩርናው ግን ለዮሴፍ ነበረ። 3 የእስራኤል በኩር የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ ነበሩ። 4 የኢዮኤል ልጆች፤ ልጁ ሸማያ፥ ልጁ ጎግ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ 5 ልጁ ሚካ፥ ልጁ ራያ፥ ልጁ ቢኤል፥ 6 የአሦር ንጉሥ ቴልጌል-ቴልፌልሶር የማረከው ልጁ ብኤራ፤ እርሱም የሮቤል ነገድ አለቃ ነበረ። 7 ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥ ዘካርያስ፥ 8 እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ ነበር፤ 9 በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ። 10 በሳኦልም ዘመን ከአጋራውያን ጋር ተዋጉ፥ እነርሱም በእጃቸው ተመትተው ወደቁ፤ በገለዓድ ምሥራቅ በኩል ባለው አገር ሁሉ በድንኳኖቻቸው ተቀመጡ። የጋድ ትውልድ 11 የጋድም ልጆች ከሮቤል ነገድ አጠገብ ባለው በባሳን ምድር እስከ ሰልካ ድረስ ተቀመጡ። 12 አንደኛው ኢዮኤል፥ ሁለተኛው ሳፋም፥ ያናይ፥ ሳፋጥ በባሳን ተቀመጡ። 13 የአባቶቻቸውም ቤቶች ወንድሞች ሚካኤል፥ ሜሱላም፥ ሳባ፥ ዮራይ፥ ያካን፥ ዙኤ፥ ኦቤድ እነርሱም ሰባት ነበሩ። 14 እነዚህም የቡዝ ልጅ የዬዳይ ልጅ የኢዬሳይ ልጅ የሚካኤል ልጅ የገለዓድ ልጅ የኢዳይ ልጅ የዑሪ ልጅ የአቢካኢል ልጆች ነበሩ። 15 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቃ የጉኒ ልጅ የአብዲኤል ልጅ አኪ ነበረ። 16 በገለዓድም ምድር በባሳን በመንደሮቹም በሳሮንም መሰማሪያዎች ሁሉ እስከ ዳርቻቸው ድረስ ተቀምጠው ነበር። 17 እነዚህ ሁሉ በትውልዶቻቸው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታም ዘመንና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመን ተቈጠሩ። 18 የሮቤልና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ፥ ጽኑዓን፥ ጋሻና ሰይፍ የሚይዙ፥ ቀስተኞችም፥ የውግያ ስልት የሚያውቁ ተዋጊዎችም፥ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ነበሩ። 19 ከአጋራውያንና ከይጡር ከናፊሽና ከናዳብ ጋር ተዋጉ። 20 በሚዋጉበትም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋልና፥ በእርሱም ታምነዋልና ተለመናቸው፤ እነርሱንም ረዳቸው፥ አጋራውያንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ሁሉ በእጃቸው ተላልፈው ተሰጡ። 21 ከእንስሶቻቸውም ኀምሳ ሺህ ግመሎች፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ሺህም በጎች፥ ሁለት ሺህም አህዮች፥ ከሰዎችም መቶ ሺህ ማረኩ። 22 ሰልፉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና ብዙ ሰዎች ተገድለው ወደቁ፤ እስከ ምርኮም ዘመን ድረስ በስፍራቸው ተቀመጡ። የምናሴ የነገድ እኩሌታ 23 የምናሴ የነገድ እኩሌታ ልጆች በምድሪቱ ተቀመጡ። ከባሳንም ጀምሮ እስከ በኣል-አርሞንዔምና እስከ ሳኔር እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በዙ። 24 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፥ ይሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝርኤል፥ ኤርምያ፥ ሆዳይዋ፥ ኢየድኤል፤ እነርሱ ጽኑዓን ኃያላን የታወቁ ሰዎች የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ነበሩ። 25 የአባቶቻቸውንም አምላክ በደሉ፥ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ባጠፋቸው በምድሩ አሕዛብ አማልክት አመነዘሩ። 26 የእስራኤልም አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌል-ቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤ የሮቤልንና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ አፈለሰ፥ እስከ ዛሬም ወዳሉበት ወደ አላሔና ወደ አቦር፥ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ አመጣቸው። |