ሉቃስ 8:13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንዲሁም በዐለት ላይ ያሉት ቃሉን በሰሙ ጊዜ በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም፥ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ ይክዳሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀውም ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ለጊዜው ነው፤ ሥር ስለሌላቸውም በፈተና ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በጭንጫም ላይ የወደቀው ሰምተው ነገሩን በደስታ የሚቀበሉት ናቸው፤ ነገር ግን ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር የላቸውም፤ መከራም በአገኛቸው ጊዜ ይክዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። |
ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ለማወቅ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝቦች እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወዳሉ።
ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያዳምጠው ነበር።
በእሾህም መካከል የወደቁት እንዲሁ ከእነዚያ ከሰሙት ወገን ናቸው፤ በመንገዳቸውም በዚህ የምድራዊ ሕይወት ምኞትና ሀብት እንዲሁም ምቾት ይታነቃሉ፤ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም።
ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝ፥ ምስጢርን ሁሉ ባውቅ፥ ዕውቀትን ሁሉ ብረዳ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።
ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት የምትጸኑ ከሆነ ነው፤ ይህም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፤ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ።
ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ “ፈታኙ ምናልባት ፈትኖአቸዋል፤ ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፤” ብዬ በመፍራት እምነታችሁን ለማወቅ ጢሞቴዎስን ላክሁ።
ይህን በምታደርግበት ጊዜ ግን እምነትንና በጎ ኅሊናን ይዘህ ይሁን፤ አንዳንዶች ሕሊናን ወደ ጎን በማድረግ፥ በእምነት ረገድ በማዕበል እንደተሰባበረች መርከብ ጠፍተዋል፤
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ፥ ዳግመኛ በእርሷ ተጠልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሯቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆንባቸዋል።
ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ነገር ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ጋር በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ እንዲገለጥ ወጡ።
እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ነውር ናቸው፥ ራሳቸውን እየመገቡ ያለ ኀፍረት ከእናንተ ጋር ይጋበዛሉ፥ በነፋስ የሚገፉ ውሃ የሌላቸው ደመናዎች፥ በበጋ ፍሬ የማያፈሩ፥ ሁለት ጊዜ የሞቱ፥ ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤