ማሕልየ መሓልይ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ የእናቴን ጡት ትጠባ ዘንድ ማን በሰጠህ? በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር። 2 ይዤ ወደ እናቴ ቤት፥ ወደ ወላጅ እናቴም እልፍኝ ባገባሁህ፥ እኔ ከመልካሙ የወይን ጠጄ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር። 3 ቀኙ ባቀፈችኝ ግራውም ከራሴ በታች በሆነች ነበር። 4 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ወድዶ እስኪነሣ ድረስ ፍቅሬን እንዳትቀሰቅሱትና እንዳታስነሡት በምድረ በዳው ኀይልና ጽንዐት አምላችኋለሁ። 5 በልጅ ወንድምዋ ላይ ተደግፋ እንደ ማለዳ ደምቃና አብርታ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ አማጠችህ፥ በዚያም ወላጅ እናትህ ወለደችህ። 6 እንደ ቀለበት በልብህ፥ እንደ ቀለበትም ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥ ቅንዐትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና። ላንቃዋ እንደ እሳት ላንቃ እንደ ነበልባል ነው። 7 ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ አይንቁትም። 8 እኅታችን ትንሽ ናት፥ ጡትም የላትም፤ ስለ እርስዋ በሚናገሩባት ቀን ለእኅታችን ምን እናድርግላት? 9 እርስዋ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሥራ፤ ደጅአፍም ብትሆን የዝግባ ሳንቃ እንሥራላት። 10 እኔ ቅጥር ነኝ፥ ጡቶችም እንደ ግንብ ናቸው፤ በዚያ ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ። 11 ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ቦታ ፍሬውን ለሚጠብቁ አከራየው፤ ሰው ሁሉ በየጊዜው ለፍሬው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ያመጣል። 12 ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፤ አንዱ ሺህ ለሰሎሞን፥ ሁለቱ መቶ ፍሬውን ለሚጠብቁ ነው። 13 በአትክልቱ ቦታ ሲኖር ሌሎች አዩት፥ ቃልህን አሰማኝ። 14 ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን ወይም የዋሊያን እንቦሳ ምሰል። |