ማሕልየ መሓልይ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ እናይሽም ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርስዋ በሩቁ እንደምትታይ እንደ ማኅበር ማሕሌት ናት። 2 አንቺ የአሚናዳብ ልጅ ሆይ፥ በጫማ አካሄድሽ እጅግ ያማረ ነው። የዳሌዎችሽ አቀማመጥ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቍዎች ይመስላል። 3 እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው። 4 ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለት መንታ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው። 5 አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፤ ዐይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በብዙዎች ልጅ በሮች አጠገብ እንዳሉ እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው። 6 በራስሽ ላይ ያለው ጠጕርሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ነው፤ የጠጕርሽም ሹርባ እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፥ ንጉሡም በሹርባው ታስሯል። 7 ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! ደስታሽንም እወድደዋለሁ። 8 ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ። 9 ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፉንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ ናቸው፥ የአፍንጫሽም ሽታ እንደ እንኮይ ነው። 10 ጕሮሮሽም ለልጅ ወንድሜ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ ለከንፈሮችና ለምላሴ እንደሚስማማ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። 11 እኔ የልጅ ወንድሜ ነኝ፥ የእርሱም መመለሻው ወደ እኔ ነው። 12 ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ፥ በመንደሮችም እንደር። 13 ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ፥ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ጡቶቼን እሰጥሃለሁ። 14 ትርንጎዎች መዓዛን ስጡ፤ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፤ ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ። |