ማሕልየ መሓልይ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም። ጠራሁት አልመለሰልኝም። 2 እነሣለሁ በከተማዪቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በገበያና በአደባባይ እፈልጋለሁ፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም። ጠራሁት አልመለሰልኝም። 3 ከተማዪቱን የሚጠብቁት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸው። 4 ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ያንጊዜ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፥ ያዝሁትም፤ ወደ እናቴም ቤት፥ ወደ ወላጅ እናቴም እልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም። 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ወድዶ እስኪነሣ ፍቅሬን እንዳትቀሰቅሱትና እንዳታስነሡት፥ በምድረ በዳው ኀይልና ጽንዐት አምላችኋለሁ። 6 መዓዛዋ እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነው፥ ከልዩ የሽቱ ቅመም ሁሉ የሆነው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ዐምድ የወጣችው ማን ናት? 7 እነሆ፥ የሰሎሞን አልጋ ናት፤ ከእስራኤል ኀያላን ስድሳ ኀያላን በዙሪያዋ ናቸው። 8 ሁሉም ሰይፍ የያዙና ሰልፍ የተማሩ ናቸው፤ በሌሊት ከሚወድቀው ፍርሀት የተነሣ ሰው ሁሉ ሰይፉ በወገቡ አለ። 9 ንጉሡ ሰሎሞን መሸከሚያን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ። 10 ምሰሶዎቹን የብር አደረገ፥ መደገፊያውንም የወርቅ፥ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ፤ ውስጡ ሰንፔር በሚባል ዕንቍ የተለበጠ ነው። ከኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ይልቅ እወድደዋለሁ። 11 እናንት የጽዮን ቈነጃጅት፥ እናቱ በሠርጉ ቀን በልቡ ደስታ ቀን ያቀዳጀችውን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን ታዩ ዘንድ ውጡ። |